Shop Amazon

Wednesday, August 22, 2018

ግልጽ ደብዳቤ ( ከሎስ አንጀልስ የአቀባበል አብይ ኮሚቴ የሕብረተሰቡ አባላት )



የተከበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ የተከበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በመጀመሪይ የከበረ ስላምታችን ይድረሳችሁ። እኛ ይህንን ጽሁፍ የምንልክላችሁ ሎስ አንጀለስ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ከአቶ ለማ መገርሳ ጋር ስትመጡ ለመቀበል ከህብረተሰቡ መሃከል፥ ከቢዝነስ፥ ከፖለቲካ ድርጅቶች፥ ከቤተክርስቲያንና ከስፖርት ድርጅቶች ተውጣጥተን በአንድ ምሽት ተደራጅተን ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ለመሥራት ተዘጋጅተን የነበርን ስብስቦች ነን።
ይህንን ስብስብ በአጭር ጊዜ ለማደራጀት የበቃነው ለዶክተር አብይ ድጋፍ በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በተጠራው ሰልፍ ላይ የቆንስላው ጽሕፈት ቤት የድጋፍ ሰልፉን አስተባባሪዎች ሊያነጋግር ይፈልጋል የሚል ነገር ተሰምቶ እነርሱ ከቆንስላ ጀነራሉ ጋር ቀጠሮ ወስደው ባደረጉት ንግግር መሰረት ነው። በንግግራቸውም ወቅት ቆንስላ ጀነራሉ አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም የጠቅላይ ሚኒስትሩና የልዑካኑ የተቀባይ ኮሚቴ ከቆንስላው ጽሕፈት ቤት ጋር ጥምረት ካላቸው ሰዎች ተውጣጥቶ እንደተቋቋመ ሲገልጹላቸው እነርሱም ሕብረተሰቡን ያላካተተ ስብስብ ተቀባይነት እንደሌለው ገለጹላቸው፥ አቶ ብርሃነም ለሃገሩ አዲስ እንደሆኑና ሕብረተሰቡን እንደማያውቁ ተናገሩ። እነዚህም ግለሰቦች እሳቸው ፈቃደኛ ከሆኑ በአጭር ጊዜ የሚችሉትን ያህል የሕብረተሰቡን አካላት ሊያሰባስቡና ሊያገናኝዋቸው ፈቃደኝነታቸውን ገልጸውላቸው ተለያዩ። እንዳሉትም በግማሽ ቀን ውስጥ 46 ግለሰቦችን አሰባስበው በአንድ የንግድ ተቋም አዳራሽ ሰብስበው ጠሯቸው።





በአዳራሹ ብዙ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ቆንስላው ባቋቋሙት የኮሚቴ አባላት ቁጥር ልክ የህብረተሰቡ ክፍል እንዲገባ ተወስኖ ነገር ግን ኮሚቴውን ማስፈቀድ እንዳለባቸው ገልጸው ተለያየን። አስፈቅደውም እኛም ልዩነታችን እንዳለ እንደተጠበቀ ሆኖ እንግዶቻችንን በሰላም በደስታ ተቀብለን ለመሸኘት ጥርሳችንን ነክሰን ገባንበት። ከዚህ ቀደም ዓይን ለዓይን ከማንተያይ አፍቃሪ ወያኔዎችና የስርአቱ አራማጆች ሆነው የተቃውሞውን ትግል በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ሊያሰናክሉ ሲሞክሩና ሲያንኳስሱ ከነበሩና ከቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ባለሟል ከሆኑ ሰዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪይ ቁጭ ብለን ተወያየን።

ቀናት እየገሰገሱ ሲሄዱ እንግዶቻችን እሁድ ልትመጡ ቅዳሜ ማታ በነበረው ስብሰባ ድረስ በመጀመሪያ ከተቋቋመው የኮሚቴ አባላት ላይ የቆንስላው ጽሕፈት ቤት ያልተካተቱ የህብረተስብብ ክፍሎች አሉ፥ የኦሮሞ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያ ድረስ አልተወከልንም ብሎ አቤቱታ አቅርቧል በሚል ሰበብ ቁጥሩን ከ 30 ወደ 40 እንዳደረሰው ተገንዝበናል። ይሄንን ሲሉ ግን እኛ በመጣንበት ቀን ብቻቸውን መጥተው ከተቀላቀሉት አንድ የኦሮሞ ይሃይማኖት መሪ ሌላ አንድም ኦሮሞ ያስገቡ አይመስለንም። በዘር የመከፋፈልና ሕዝብን የመለያየት ዘዴ ፋሽኑ አልፎበታል የሚል አመራር አካል ኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ቁጭ ብሎ የኢትዮጵያ ወኪል ተብለው እዚህ ሎስ አንጅለስ ከተማ የተቀመጡት አሳፋሪ ሰዎች ግን እዚህ ያለውን ሰው በዘርና በሃይማኖት ኮታ ሲያወዛግቡት ከርመዋል። በተለምዶ አነጋገር ዘር ይበሉት እንጂ እኛ የሰው ዘር አንድ ብቻ መሆኑንና ልዩነቱ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እናውቃለን። ይሄ ሁሉ ነገር ሲካሄድ ግን እየተመለከትን ሕብረተሰቡ ተስፋ ቆርጦ የቀዘቀዘ አቀባበል እንዳይሆን የተቻለንን ጥረት አድርገናል ከኛ ዜና የሚጠብቀውንም ማሕበረሰብ እንዳይቆጣና አቀባበሉ እክል እንዳይገጥመው ንግግራችን እንዳይዛነፍ ትልቅ ጥንቃቄ አድርግናል።
ከዚህ ቀደም የቆንስላው ጽህፈት ቤት ካቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ እዚህ ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ ሰው እንደሌለ ተቆጥሮ እነኝህ የዘር በሽታ የተጠናወታቸው ሰዎች ከዚህ በፊት የቀድሞው መንግሥት ተወካዮች ሲመጡ የምትጠራ ሴት ሳንዲያጎ ከምትባል በሁለት ሰዓት ርቀት ላይ ከምትገኝ ከተማ ተጠርታ በሳምንት ሁለት ሶስቴ የምትመላለስ event planner ነበረች። ይህች ግለሰብ እኛ ከመግባታችን በፊት ምን ዓይነት የመሰብሰቢያ አዳራሾች ፈልጋ እንደነበረ አልተገለጸልንም። ከገባን በኋላ ግን አገኘች ተብሎ 15 ሺህ ሰው ይችላል የተባለው አዳራሽ እውነቱን ስናውቀው ግን ግፋ ቢል ከ12 እስከ 13 ሺህ ብቻ ከመቻሉም ሌላ፥ ከኢትዮጵያ የመጡት ልዑካን ለጠቅላይ ሚኒስትር መቀበያ የማይመጥን ስፍራ ሆኖ አግኝተውት በተጭማሪ ደግሞ ዋጋው ከተሰጠን በጀት ጋር ተመጣጥኝ ሳይሆን ቀርቶ፥ ተቋሙም ካነጋገረን በኋላ ለሴክዩሪቲ እንደማያመች ተገንዝቦ ቦታው ሊሰረዝ በቅቷል። ሌላ አዲስ የተገነባ 22 ሺህ ሰው የሚይዝ ደረጃውን የጠበቀ ሁሉን ያካተተ ስፍራ በአንዲት ተጽእኖ ፈጣሪ በሆነች የሎስ አንጀለስ ነዋሪ እህታችን አማካኝነት ተገኝቶ ልዑካኑም ወደውት ሲያበቃ ዋጋው ተቀንሶ እንኳን $600 ሺህ ዶላር ስለሆነ እንዲቀር ተገደድን።





በመጨረሻም አቀባበል የተደረገበት አዳራሽ በሌላ ተጽእኖ ፈጣሪ ኢትዮፕያዊት በመጨረሻዎቹ ቀናት ስላገኘችልን አመስግነናት ስንዘጋጅ ከረምን። ይህችን ግለስብ ከሌሎቻችን የሚለያት ተጽእኖ ፈጣሪነቷ በአሉታዊ መልኩ ይህንን ዥግጅት ለማስተባበር በተቋቋመው ኮሚቴ ላይ ጭምር ነበር። ግለሰቧበሃካል ስብሰባችን ላይ ባትገኝም በቋንቋ ችግር ይሁን በሌላ ባልታወቀ ምክንያት የቆንስላውን ጽህፈት ቤት ወክላ ውል የምትዋዋለው ከባለስልጣኖችም ጋር በሚደረግ ስብሰባ ላይ ቆንስላ ጀነራሉ ቁጭ ባሉበት እርሷ የእሳቸው አፍ ሆና ውሳኔ ሰጪ መሆንዋና ኮሚቴው ቀን ተሌት ተሰብስቦ የወሰነውን ውሳኔ ቆንስላ ጀነራሉ ከአንድ ስልክ ጥሪ በኋላ አይ እሷ እንዲህ ስላለች እንዲህ ነው የሚሆነው ማለታቸው ሁላችንንም ያስገረመ ክስተትና የአሰራር ሂደት ነበረ።
የመግቢያ ትኬቱን በተመለከተ ቀድሞ የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት በ 14 ከተሞች ውስጥ የቀደመ ትውውቅ ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረው መዝግበዋቸው ለሌላው ሕብረተሰብ የማይዳረስበት ሁኔታ ስለታየን እስከ መጨረሻው ቀን ሰው ሁሉ ከተማ ውስጥ ከገባ በኋላ ተሰልፎ ቀድሞ የመጣ ቀድሞ የመግባት እድል እንዲኖረው ለማድረግ ያላሰለስ ጥረት አድርገን ነበር። ነገር ግን ከላይ እንደጠቀስነው አሉታዊ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነችው ግለሰብ ውል ከተዋዋለችው ተቋምና ከቆንስላው ጽህፈት ቤት ጋር ባላት የጠበቀ ግንኙነት በተሰጣት ሙሉ መብት መሰረት መግቢያው ትኬት ባልጠበቅነውና ባላሰብነው መንገድ እጇ ገባ። ኮሚቴው 150 ወጣቶችንና 20 የሚሆኑ የሴክዩሪቲ ኮሚቴ አባላትን ከ7 am ጀምሮ ትኬቱን እንዲያድሉ ውሳኔ ቢያስተላልፍም እሷና መሰሎቿ ከተመደቡት ሰዎች በፊት ማለትም ከ 6 am በፊት ጀምረው ትኬቱን ሲያድሉ ብሎም 2500 ትኬት ይላክ በተባለው በሊትል ኢትዮጵያ አካባቢ በራሷ ውሳኔ 800 ትኬት ብቻ በመላኳ ረብሻ ተፈጥሮ የሬስቶራንት ባለቤቶች ፖሊስ ለመጥራት ተገደዋል።


ፈጣሪ ጠበቀንና በረደ እንጂ ብዙ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያን እንግዶቻቸውን ለመቀበል በጉጉት ጠብቀው ሳለ ከቦታው ማነስና ትኬቱን በማደል ላይ በተፈጠረው ውዥንብር ሊመጡ የዓመት እረፍታቸውን የወሰዱ በአሪዞና፥ በሳንዲያጎ፥ በሲያትል፥ በኮሎራዶ፥ በላስ ቬጋስና በሌሎችም ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በርካታ ሰዎች ተስፋ በመቁረጥ ጉዟቸውን ሰርዘው እንደቀሩና ሎስ አንጀለስም ድረስ ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው አዳራሹ መግባት አቅቷተው እያለቀሱ እንደተመለሱ ተነግሮናል። ከአዳራሹ ለሚተርፈውም ሰው በብዙ ወጪ ወደተዘጋጀው አዳራሽ እንኳ ሳይገቡ በንዴት ተመልሰዋል። ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አዳራሹ ስንገባ ለሴክዩሪቲ ተብሎ የተገደበው ረድፍ በሰው ተሞልቶ ሌሎች አካባቢዎች ግን ባዶ ሆነው ታይተዋል። ለኮሚቴው አባላት ግን የተነገረው ትኬቱ ታድሎ እንዳለቀ ነበረ። በሚገርም ሁኔታ ግን በየጢሻው ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትኬቶች ተጥለው እንደተገኙ በምስል ተቀርጾና ጥቂቱም በኮሚቴ አባላት እጅ ገብቷል። 

ይህች ግለሰብ ግን በመድረክም ሆነ በጽሁፍ ልዩ ሙገሳ ተደርጎላታል። ይሄ ነገር መጀመሪያ እንደጠረጠርነው 1. ትኬቱን ሁሉ አግበስብሰው ወስደው እንግዶቻችን ባዶ አዳራሽ እንዲጠብቃቸው ታስቦ ይሆን? ወይስ 2. ትኬቱን ለካድሬዎቻቸውና ለአፍቃሪ ወያኔ ግለሰቦች አድለው አዳራሹ ውስጥ hostile environment ለመፍጠር አስበው ይሆን? ይሄንን ሊያውቁ የሚችሉት የቆንስላው ጽህፈት ቤት የተወሰኑ ሠራተኞች፥ አጫፋሪዎቻቸው የቀድሞ ሥርዓት አራማጆችና አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው። አዳራሹም በገባንበት ሰዓት በፕሮቶኮልና በሴክዩሪቲ ኮሚቴ የተመደቡት የሕብረተሰቡ ክፍል የኮሚቴ አባላት አሁን ሥራ የላችሁም ቁጭ በሉ መባላቸውና የቀድሞው ኮሚቴ አባላት እንደ ሰፈር አለቃ ውር ውር ማለታቸውስ ከዚህ ሴራ ጋር የተያያዘ ይሆን? ብሎስ የፕሮቶኮሉን ኮሚቴ ይመሩ የነበሩት የቆንስላው ጽህፈት ቤት ሠራተኛ ወይዘሮ በድንገት መሰወርስ ምን ሚና ተጫውቶ ይሆን?
የማታውን እራት በተመለከተ ኮሚቴው የተነገረው ግብዣው የምስጋና ግብዣ ሲሆን ተጋባዦቹ የአዘጋጅ ኮሚቴው አባላት ከነባለቤቶቻቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካኑ ፥ የሃይማኖት አባቶችና፥ የቆንስላው ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ከነባለቤቶቻቸው በጠቅላላው ቤቱ የሚችለው 300 ስዎች ብቻ እንደሆነ ነበር። ሰዓቱ ሲደርስ በተጨባጭ የታየው ግን በቦታው ያልነበሩ አይተናቸው ከየት እንዴት እንደመጡ የማናውቃችው ግለሰቦች ከገቡ በኋላ በሩን በግዜ በመዝጋት የዋናው ኮሚቴ አባላትን ውጪ አስቀርተዋል። ከዚያም የቆንስላው ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ የሆኑ ግለሰብ በር ላይ ሄደው የኮሚቴውን አባላት በዓይናቸው እያዩ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ማለትም የቀድሞው ኮሚቴ አባላትን ብቻ እየመረጡ እያስገቡ ሌሎቹን ግን ከአንድ ዲፕሎማት በማይጠበቅ ሁኔታ እየተሳደቡ እንዳይገቡ እንዳደረጓችው በሚያሳዝን ሁኔታ በገሃድ ታይቷል። መቼም ማንም የኮሚቴው አባላት ከእንግዶቹ ጋር ጥቂት ጊዜ ለማሳለፍ፥ ለመተዋወቅና የኢትዮጵያ አመራር አካል ለ27 ዓመታት የነበረውን የጨለማ ዘመን ብርሃን የፈነጠቁበትን ግለሰቦች ለማመስገን እንጂ እራት ለመብላት እዚያ ስፍራ እንዳልመጣ የታወቀ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካኑ እራት ሳይበሉና የመድረክ ዝግጅቱ ሳያልቅ መሄዳችው እጅግ ቢያሳዝነንም ውስጥ ያሉት ሰዎች በኮሚቴው ውሳኔ ከተጋበዙት ሰዎች ውጭ መሆንና ዋናው ተጋባዦች ላይ በር ተዘግቶባቸው በነበረ ሁኔታ ግን ቢቆዩ ችግር ሊፈጠር ይችል ስለነበረ በጊዜ መሄዳቸው አስደስቶናል። ይሄ ህኔታ ከደህንንታችሁ አንጻር በስብሰባችን ውስጥ በመጨረሻዎቹ ቀናት አይተናቸው የማናውቃቸው የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ተቀጣሪዎችና ሌሎችም አዳዲስ ፊቶች ብቅ ማለት፥ ከኢትዮጵያ የመጡትን ጋዜጠኞች መታወቂያ አዘጋጅቶ የመስጠት ሃላፊንቷን ዘንግታ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚናገሩበት ሰዓት ሴክዩሪቲውን አልፋ በሚያሳፍር ሁኔታ በጀርባቸው በመጋረጃ ብቅ ጥልቅ ከምትለው ግለሰብ ጀምሮ በጣም አሳስቦን ስለነበረ ከሴክዩሪቲ አንጻር እራቱም ላይ ያሉት ሰዎች ማን እንደሆኑና ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስለማናውቅ ራቱን ትታችሁ መሄዳችሁ ከአደጋ አድኖናል ለማለት ይስደፍረናል። እናንተ ከወጣችሁ በኋላ ግን ተስፋ ቆርጠው ቤታቸው ያልሄዱትን አንዳንድ የኮሚቴ አባላት ግቡና ብሉ እንዳሏቸው ተመልክተናል። ይሄ ለራሳቸው ዜጋ ያላቸውን ትልቅ ንቀት ያሳያል።






ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተፈጠረው ሁኔታ ግን ትዝብትን ከመፍጠሩም ሌላ ያሳየን ነገር ቢኖር አንደኛ ከሕብረተሰቡ ተውጣጥቶ የመጣው ስብስብ በስም እንጂ በተግባር እውነተኛ የኮሚቴ አባል እንዳልነበረና ሲሸነግል እንደከረመ። ውህደት የተባለው የዘይትና የውሃ ውህደት እንደነበረ፤ ሁለተኛ የቆንስላው ጽሕፈት ቤት ከሕብረተሰቡ ጋር መዋሃድ ከልቡ አለመፈልጉንና በፊት በጥቅማጥቅም ከነሱ አካባቢ ከሚያንዣብቡ ግለሰቦች ጋር ብቻ ለመሥራት እንደሚፈልጉ፤ ሦስተኛ የአንዲት ሉዓላዊት ሃገር ወኪሎች ያሳዩት የስነምግባር ጉድለት አሳፋሪ መሆኑን፥ የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ደካማ አመራር እንዳለውና አንዳንዶቹ ግለሰቦቹ ለቦታው የማይመጥኑ መሆናቸውን ነው ።
የተከበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ፥ የተከበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ፥ ይህንን እናንተን ለመቀበል የሄድንበትን ሂደት ለናንተ ያካፈልናችሁ በጣም ጥቂቱን ቅንጫቢውን ሲሆን ምክንያታችን ኢትዮጵያን የምታህል ሃገር ወክለው በሎስ አንጀለስ ከተማ ያሉትን ለቦታው ብቃት የሌላቸውን ግለሰቦች ቢቻል ለቦታው በሚመጥኑ ሰዎች መተካት ባይቻል ደግሞ ትምህርት ቤት ገብተው ለቦታው የሚይስፈልገውን ስልጠናና በእግረመንገዳቸውም የቋንቋ ስልጠና ቢሰጣቸው ብለን ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ለወያኔ ሥርዓት ጎምበስ ቀና ሲሉ የነበሩ አሁንም ከቆንስላው ጽህፈት ቤት ጋር ባላቸው ቁርኝት አንዳንድም ከህብረተሰቡ ጋር በአካል የማይተዋወቁ ነገር ግን በነዚህ ግለሰቦች የሚጠለፉ ንጹሃን ዜጎች ስላሉ እነኝህን በሁለት ቢላ የሚበሉ ስግብግቦች በፊት እንደለመዱት አሁንም የለውጡ ገጽታ ለመሆን እየተፍጨረጨሩና ለለውጡ ብዙ መስዋእትነት የከፈሉትን ሰዎች በማግለል እንዳይሰማሩ እንዲታሰብበት በማለት ነው።
ጊዜአችሁን ወስዳችሁ ስሞታችንን ስለሰማችሁ በጣም እናመሰግናለን ይገባል የምትሉትን እርምጃ እንደምትወስዱ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይባርክ ለሃገራችን ሰላምን ፥ ፍቅርን፥ መተሳሰብንና አንድነትን ያድልልን።
ከሕብረተሰቡ ተውጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴ
ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
Source Abay Media 






No comments:

Post a Comment