ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 1
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
2 ፤ ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
3 ፤ እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
6 ፤ እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።
8 ፤ እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
9 ፤ እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።
10 ፤ እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
11 ፤ እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።
12 ፤ ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
13 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።
14 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤
15 ፤ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
17 ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
18 ፤ በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
19 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።
20 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
22 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።
23 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።
24 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።
25 ፤ እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
26 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።
27 ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28 ፤ እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
29 ፤ እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤
30 ፤ ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።
31 ፤ እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።
ምዕራፍ 2
ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ።
2 ፤ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።
4 ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ አምላክ ሰማይንና ምድርን ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው።
5 ፤ የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤
6 ፤ ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር።
7 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።
8 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።
9 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
10 ፤ ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።
11 ፤ የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤
12 ፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል።
13 ፤ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።
14 ፤ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው።
15 ፤ አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።
16 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
17 ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።
18 ፤ እግዚአብሔር አምላክም አለ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።
19 ፤ እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።
20 ፤ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር።
21 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።
22 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።
23 ፤ አዳምም አለ። ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።
24 ፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25 ፤ አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።
ምዕራፍ 3
እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም። በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።
2 ፤ ሴቲቱም ለእባቡ አለችው። በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤
3 ፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ። እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም።
4 ፤ እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም፤
5 ፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።
6 ፤ ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።
7 ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።
8 ፤ እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።
9 ፤ እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ። ወዴት ነህ? አለው።
10 ፤ እርሱም አለ። በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም።
11 ፤ እግዚአብሔርም አለው። ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?
12 ፤ አዳምም አለ። ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።
13 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን። ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም አለች። እባብ አሳተኝና በላሁ።
14 ፤ እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው። ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ።
15 ፤ በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።
16 ፤ ለሴቲቱም አለ። በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።
17 ፤ አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤
18 ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።
19 ፤ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።
20 ፤ አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና።
21 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም።
22 ፤ እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤
23 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ።
24 ፤ አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።
ምዕራፍ 4
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም። ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች።
2 ፤ ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።
3 ፤ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤
4 ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤
5 ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?
7 ፤ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።
8 ፤ ቃየንም ወንድሙን አቤልን። ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።
9 ፤ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ። አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?
10 ፤ አለውም። ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።
11 ፤ አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።
12 ፤ ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።
13 ፤ ቃየንም እግዚአብሔርን አለው። ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት።
14 ፤ እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።
15 ፤ እግዚአብሔርም እርሱን አለው። እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።
16 ፤ ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።
17 ፤ ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፥ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት።
18 ፤ ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ።
19 ፤ ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ።
20 ፤ ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ።
21 ፤ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ።
22 ፤ ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች።
23 ፤ ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው። እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፥ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፥ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤
24 ፤ ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ። ይበቀሉታል
25 ፤ አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም። ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው።
26 ፤ ለሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ። a
ምዕራፍ 5
የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤
2 ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው።
3 ፤ አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው።
4 ፤ አዳምም ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
5 ፤ አዳምም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
6 ፤ ሴትም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሄኖስንም ወለደ፤
7 ፤ ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
8 ፤ ሴትም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
9 ፤ ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ፥ ቃይናንንም ወለደ፤
10 ፤ ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አሥራ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
11 ፤ ሄኖስም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምስት ዓመት ሆነ ሞተም።
12 ፤ ቃይናንም መቶ ሰባ ዓመት ኖረ፥ መላልኤልንም ወለደ፤
13 ፤ ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አርባ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
14 ፤ ቃይናንም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥር ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
15 ፤ መላልኤልም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ያሬድንም ወለደ፤
16 ፤ መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
17 ፤ መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
18 ፤ ያሬድም መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሄኖክንም ወለደ
19 ፤ ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ የኖረው ስምንት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
20 ፤ ያሬድም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
21 ፤ ሄኖክም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ማቱሳላንም ወለደ፤
22 ፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ ማቱሳላንም ከወለደ በኋላ የኖረው ሁለት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
23 ፤ ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ።
24 ፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።
25 ፤ ማቱሳላም መቶ ሰማኒያ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ላሜሕንም ወለደ፤
26 ፤ ማቱሳላም ላሜሕን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
27 ፤ ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
28 ፤ ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ።
29 ፤ ስሙንም። እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።
30 ፤ ላሜሕም ኖኅን ከወለደ በኋላ የኖረው አምስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
31 ፤ ላሜሕ የኖረበት ዘመን ሁሉ ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
32 ፤ ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።
-----
ምዕራፍ 6
እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤
2 ፤ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።
3 ፤ እግዚአብሔርም። መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ።
4 ፤ በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።
5 ፤ እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ።
7 ፤ እግዚአብሔርም። የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ።
8 ፤ ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።
9 ፤ የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።
10 ፤ ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።
11 ፤ ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።
12 ፤ እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።
13 ፤ እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።
14 ፤ ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፥ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።
15 ፤ እርስዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን።
16 ፤ ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመትዋም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ።
17 ፤ እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል።
18 ፤ ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ።
19 ፤ ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን።
20 ፤ ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ።
21 ፤ ከሚበላውም መብል ሁሉ ለአንተ ውሰድ፥ ወደ አንተም ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተም ለእነርሱም መብል ይሆናል።
22 ፤ ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። a
ምዕራፍ 7
እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።
2
3 ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባትና እንስት፥ ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ።
4 ፤ ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና።
5 ፤ ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ።
6 ፤ ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።
7 ፤ ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ።
8 ፤ ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥
9 ፤ እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።
10 ፤ ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ።
11 ፤ በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤
12 ፤ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ።
13 ፤ በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ።
14 ፤ እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥
15 ፤ ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።
16 ፤ ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት።
17 ፤ የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ፤ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች።
18 ፤ ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች።
19 ፤ ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።
20 ፤ ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ተራሮችም ተሸፈኑ።
21 ፤ በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ።
22 ፤ በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።
23 ፤ በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ።
24 ፤ ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።
ምዕራፍ 8
እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ፤
2 ፤ የቀላዩም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፥ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤
3 ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ።
4 ፤ መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።
5 ፤ ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ።
6 ፤ ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥
7 ፤ ቁራንም ሰደደው፤ እርሱም ወጣ፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።
8 ፤ ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት።
9 ፤ ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፥ ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት።
10 ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ።
11 ፤ ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ።
12 ፤ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
13 ፤ በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅም የመርከቢቱን ክዳን አነሣ፥ እነሆም፥ ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ።
14 ፤ በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ደረቀች።
15 ፤ እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው።
16 ፤ አንተ ሚስትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ።
17 ፤ ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ።
18 ፤ ኖኅም ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወጣ፤
19 ፤ አራዊት ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ ወፎችም ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚርመሰምሰው ሁሉ በየዘመዳቸው ከመርከብ ወጡ።
20 ፤ ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።
21 ፤ እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ። ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።
22 ፤ በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።
ምዕራፍ 9
እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው። ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት።
2 ፤ አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል።
3 ፤ ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ።
4 ፤ ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፤
5 ፤ ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ።
6 ፤ የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።
7 ፤ እናንተም ብዙ፥ ተባዙ፤ በምድር ላይ ተዋለዱ፥ እርቡባትም።
8 ፤ እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ።
9 ፤ እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤
10 ፤ ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል።
11 ፤ ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
12 ፤ እግዚአብሔርም አለ። በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤
13 ፤ ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።
14 ፤ በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤
15 ፤ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
16 ፤ ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።
17 ፤ እግዚአብሔርም ኖኅን። በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።
18 ፤ ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው።
19 ፤ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች።
20 ፤ ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ።
21 ፤ ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ።
22 ፤ የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
23 ፤ ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም።
24 ፤ ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።
25 ፤ እንዲህም አለ። ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
26 ፤ እንዲህም አለ። የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
27 ፤ እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
28 ፤ ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ።
29 ፤ ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
ምዕራፍ 10
የኖኅ ልጆች የሴም የካም የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ ከጥፋት ውኃም በኋላ ልጆች ተወለዱላቸው።
2 ፤ የያፌት ልጆች ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ ያዋን፥ ይልሳ፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ ናቸው።
3 ፤ የጋሜርም ልጆች አስከናዝ፥ ሪፋት፥ ቴርጋማ ናቸው።
4 ፤ የያዋንም ልጆች ኤሊሳ፥ ተርሴስ፥ ኪቲም፥ ሮድኢ ናቸው።
5 ፤ ከእነዚህም የአሕዛብ ደሴቶች ሁሉ በየምድራቸው በየቋንቋቸው በየነገዳቸው በየሕዝባቸው ተከፋፈሉ።
6 ፤ የካምም ልጆች ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው።
7 ፤ የኩሽም ልጆች ሳባ፥ ኤውላጥ፥ ሰብታ፥ ራዕማ፥ ሰበቃታ ናቸው። የራዕማ ልጆችም ሳባ፥ ድዳን ናቸው።
8 ፤ ኩሽም ናምሩድን ወለደ፤ እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆንን ጀመረ።
9 ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም። በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደ ናምሩድ ተባለ።
10 ፤ የግዛቱም መጀመሪያ በሰናዖር አገር ባቢሎን፥ ኦሬክ፥ አርካድ፥ ካልኔ ናቸው።
11 ፤ አሦርም ከዚያች አገር ወጣ፤ ነነዌን፥ የረሆቦትን ከተማ፥ ካለህን፥
12 ፤ በነነዌና በካለህ መካከልም ሬሴንን ሠራ፤ እርስዋም ታላቂቱ ከተማ ናት።
13 ፤ ምጽራይምም ሉዲምን፥ ዐናሚምን፥ ላህቢምን፥ ነፍታሌምን፥ ፈትሩሲምን፥
14 ፤ ከእነርሱ የፍልስጥኤም ሰዎች የወጡባቸውን ከስሉሂምን፥ ቀፍቶሪምንም ወለደ።
15 ፤ ከነዓንም የበኵር ልጁን ሲዶንን፥ ኬጢያውያንንም፥
16 ፤ ኢያቡሳውያንንም፥ አሞራውያንንም፥
17 ፤ ጌርጌሳውያንንም፥ ኤዊያውያንንም፥
18 ፤ ዐሩኬዎንንም፥ ሲኒንም፥ አራዴዎንንም፥ ሰማሪዎንንም፥ አማቲንም ወለደ። ከዚህም በኋላ የከነዓናውያን ነገድ ተበተኑ።
19 ፤ የከነዓናውያንም ወሰን ከሲዶን አንሥቶ ወደ ጌራራ በኩል ሲል እስከ ጋዛ ድረስ ነው፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ፥ ወደ አዳማና ወደ ሰቦይም በኩልም ሲል እስከ ላሣ ድረስ ነው።
20 ፤ የካም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራችውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው።
21 ፤ ለሴምም ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የያፌት ታላቅ ወንድምና የዔቦር ልጆች ሁሉ አባት የሆነ ነው።
22 ፤ የሴምም ልጆች ኤላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ፥ አራም ናቸው።
23 ፤ የአራምም ልጆች ዑፅ፥ ሁል፥ ጌቴር፥ ሞሶሕ ናቸው።
24 ፤ አርፋክስድም ቃይንምን ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን፥ ሳላም ዔቦርን ወለደ።
25 ፤ ለዔቦርም ሁለት ልጆች ተወለዱለት፤ የአንደኛው ስሙ ፋሌቅ ነው፥ ምድር በዘመኑ ተከፍላለችና፤ የወንድሙም ስም ዮቅጣን ነው።
26 ፤ ዮቅጣንም ኤልሞዳድን፥ ሣሌፍንም፥ ሐስረሞትንም፥
27 ፤ ያራሕንም፥ ሀዶራምንም፥ አውዛልንም፥
28 ፤ ደቅላንም፥ ዖባልንም፥ አቢማኤልንም፥
29 ፤ ሳባንም፥ ኦፊርንም፥ ኤውላጥንም፥ ዩባብንም ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው።
30 ፤ ስፍራቸውም ከማሴ አንሥቶ ወደ ስፋር ሲል እስከ ምሥራቅ ተራራ ድረስ ነው።
31 ፤ የሴም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው።
32 ፤ የኖኅ የልጆቹ ነገዶች እንደ ትውልዳቸው በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። አሕዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከእነዚህ ተከፋፈሉ።
ምዕራፍ 11
ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።
2 ፤ ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ።
3 ፤ እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፋት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው።
4 ፤ እንዲህም። ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።
5 ፤ እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።
6 ፤ እግዚአብሔርም አለ። እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም።
7 ፤ ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።
8 ፤ እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ።
9 ፤ ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።
10 ፤ የሴም ትውልድ ይህ ነው። ሴም የመቶ ዓመት ሰው ነበረ፥ አርፋክስድንም ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ወለደ።
11 ፤ ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
12 ፤ አርፋክስድም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ቃይንምንም ወለደ፤
13 ፤ አርፋክስድም ቃይንምን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። ቃይንምም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሳላንም ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን ከወለደ በኋላ ሶስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
14 ፤ ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ዔቦርንም ወለደ፤
15 ፤ ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
16 ፤ ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፥ ፋሌቅንም ወለደ፤
17 ፤ ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
18 ፤ ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ራግውንም ወለደ፤
19 ፤ ራግውንም ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
20 ፤ ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሴሮሕንም ወለደ፤
21 ፤ ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
22 ፤ ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ናኮርንም ወለደ፤
23 ፤ ናኮርንም ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
24 ፤ ናኮርም መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ታራንም ወለደ፤
25 ፤ ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
26 ፤ ታራም መቶ ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ።
27 ፤ የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ።
28 ፤ ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ።
29 ፤ አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው።
30 ፤ ሦራም መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም።
31 ፤ ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ።
32 ፤ የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።
ምዕራፍ 12
እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።
2 ፤ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤
3 ፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።
4 ፤ አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።
5 ፤ አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።
6 ፤ አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና። ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ።
8 ፤ ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ።
9 ፤ አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ።
10 ፤ በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና።
11 ፤ ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት። አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ
12 ፤ የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ። ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል።
13 ፤ እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ። እኅቱ ነኝ በዪ።
14 ፤ አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤
15 ፤ የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት።
16 ፤ ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረገለት፤ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም ነበሩት።
17 ፤ እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ።
18 ፤ ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም?
19 ፤ ለምንስ። እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፤ ይዘሃት ሂድ።
20 ፤ ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው።
ምዕራፍ 13
አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ።
2 ፤ አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ።
3 ፤ ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤
4 ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
5 ፤ ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው።
6 ፤ በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም።
7 ፤ የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር።
8 ፤ አብራምም ሎጥን አለው። እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ።
9 ፤ ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።
10 ፤ ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ።
11 ፤ ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ።
12 ፤ አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ።
13 ፤ የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።
14 ፤ ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው። ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤
15 ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና።
16 ፤ ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል።
17 ፤ ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና።
18 ፤ አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።
ምዕራፍ 14
በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ፤
2 ፤ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ።
3 ፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው።
4 ፤ አሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ።
5 ፤ በአሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፤
6 ፤ የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ።
7 ፤ ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፤ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴሶን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ።
8 ፤ የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤
9 ፤ የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ።
10 ፤ በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራራ ሸሹ።
11 ፤ የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ።
12 ፤ በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።
13 ፤ አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የአድባር ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር።
14 ፤ አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ።
15 ፤ ብላቴኖቹንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው።
16 ፤ ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።
17 ፤ ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ።
18 ፤ የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ።
19 ፤ ባረከውም። አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤
20 ፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።
21 ፤ የሰዶም ንጉሥም አብራምን። ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው።
22 ፤ አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው። ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤
23 ፤
24 ፤ አንተ። አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፤ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ።
No comments:
Post a Comment