የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተሩ ቴድሮስ አድሐኖምን በተመለከተ ቅሬታ እንዳለውና ደስተኛ አለመሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ዶክተር ቴድሮስ በአገሪቱ ውስጥ ምን እንደተከሰተ ከመንግሥት በኩል ለመረዳት አለመሞከራቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ቴድሮስ "አንዳንድ በሮችን ማንኳኳታቸውን" መንግሥት እንደሚያውቅ አመልክተው ይህንንመ በተመለከተ መንግሥት በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት ይወስናል ሲሉ ተናግረዋል።
በተያያዘም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክትር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው ህወሓትን የሚደግፍ የማግባባት ሥራ አከናውነዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከሰሱ።
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ መሰደዳቸው እየተነገረ ነው።
ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ከመሆናቸው በፊት በህወሓት በሚመራው መንግሥት ወቅት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።
ቢቢሲ ዋና ዳይሬክተሩ ላይ የቀረበውን ክስ አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አልሰጡም
የአገሪቱ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ህወሓትን ለመደገፍና የጦር መሳሪያ እንዲያገኝ ለማድረግ ዶ/ር ቴድሮስ "ያልፈነቀሉት ድናጋይ የለም"።
"ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመው እነዚህን ሰዎች ያወግዛሉ ብለን አንጠብቅም። እነሱን ለመደገፍ ሁሉንም ነገር ሲያደርጉ ነበር፤ ጎረቤት አገራት ጦርነቱን እንዲያወግዙ ሲቀሰቅሱ ነበር" ብለዋል ጀነራል ብርሃኑ።
"የጦር መሳሪያ እንዲያገኙ ሲሰራላቸው ነበር" ብለዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ቴድሮስ፤ የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ዕውቅናን አግኝተዋል።
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ ሁለት ሳምንት አልፎታል።
No comments:
Post a Comment