በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት በወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ ዝርዝር ውስጥ ከገቡት የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ የስድስተኛነትን ቦታ ስትይዝ በዓለም 60ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣላች።
የተለያዩ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የአገራትን ወታደራዊ ጥንካሬ የሚያሳይ ደረጃን የሚያወጣው 'ግሎባል ፋየር ፓወር' የተባለው ተቋም ለዚህ ዓመት ባወጣው ዝርዝር ውስጥ 35 የአፍሪካ አገራት የተካተቱ ሲሆን ኢትዮጵያ የ6ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በደረጃው ሰንጠረዥ መሠረት ግብጽ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን፣ በመከተል ደግሞ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮና ኢትዮጵያ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል። የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ደግሞ በ10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
ግሎባል ፋየር ፓወር በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት መካከል ባደረገው የወታደራዊ ጥንካሬ ምዘና፣ ከ50 በላይ መመዘኛዎችን የተጠቀመ ሲሆን በዚህም አገራት ያላቸውን የወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ በዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ድርጅቱ የ138 አገራት ወታደራዊ ጥንካሬን የመዘነ ሲሆን፣ በዓለም በወታደራዊ ኃይላቸው ኃያላን ተብለው በቀዳሚነት የተቀመጡት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከአንድ አስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ በ60ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ግብጽ በ13ኛ ደረጃ፣ ሱዳን ደግሞ በ77ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ደረጃውን ያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር የየአገራቱን ወታደራዊ የሰው ኃይል፣ ከታጠቁት መሳሪያዎች ጋር በማቅረብ አነጻጽሮ ነው የዓለም አገራትን ወታደራዊ ኃይል ደረጃን ይፋ ያደረገው።
በያዝነው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት በዝርዝሩ ውስጥ የ138 አገራት ወታደራዊ ኃይል የተገመገመ ሲሆን፤ የእያንዳንዱ አገር ወታደራዊ አቋም ከተራዘመ የማጥቃትና የመከላከል ወታደራዊ ዘመቻ አቅም አንጻር በተለያዩ መመዘኛዎች ተግምግሞ ነው በግሎባል ፋየር ፓወር ደረጃ የተሰጠው።
የዓመቱ የአገራት ወታደራዊ አቅም ደረጃ ዝርዝር ሲወጣ፣ የሕዝብ ብዛት፣ የሠራዊት መጠን፣ የታጠቁት መሣሪያ፣ የገንዘብ አቅም፣ የአቅርቦት ብቃትና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን ጨምሮ ከ50 በላይ መመዘኛዎችን ተጠቅሟል ተብሏል።
በዚህ ዓመቱ የአገራት ወታደራዊ አቅም አመላካች ዝርዝር ውስጥ ከ35 የአፍሪካ አገራት 6ኛ፣ ከ138 የዓለም አገራት መካከል ደግሞ በ60ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ፣ ካላት 108 ሚሊዮን ሕዝብ አንድ በመቶው ወይም 162 ሺህ የሚሆነው በሠራዊት አባልነት ታቅፏል ተብሏል።
በሠራዊት ብዛት የኢትዮጵያ ሠራዊት 162 ሺህ ወታደሮች ሲኖሯት፣ 24 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 8 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 365 ታንኮች፣ 130 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ 480 ከባድ መድፎች፣ 180 የሮኬት መተኮሻዎች እንዲሁም 65 ቀላል መድፎች ሲኖሩት የአገሪቱ ዓመታዊ ወታደራዊ በጀት ደግሞ 520 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ግሎባል ፋየር ፓወር ገልጿል።
ከዚህ አንጻር በአህጉረ አፍሪካ በወታደራዊ ኃይል ቀዳሚ የሆነችው ግብጽ ከ104 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን፣ አጠቃላይ የወታደር ብዛቷ ደግሞ 930 ሺህ፣ ታዋጊ አውሮፕላን 250፣ ተዋጊ ሄሊኮፕተር 91፣ ታንኮች 3735፣ ከባድ መድፍ 2200፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች 11ሺህ ሲኖራት፣ 10 ቢሊዮን ዶላር የመከላከያ በጀቷ እንደሆነ የደረጃው ሰንጠረዥ አመልክቷል።
ከ138 አገራት መካከል በ77ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሱዳን ከ45 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሲኖራት፣ አጠቃላይ ያላት ወታደር ብዛት 190 ሺህ ነው። በትጥቅ በኩል 45 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 43 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 830 ታንኮች፣ 450 ብረት ለበስ ተሽከርካሪ አላት። የአገሪቱ ዓመታዊ የመከላከያ በጀት 4 ቢሊየን ዶላር ነው።
በአፍሪካ አህጉር ግብጽ በወታደራዊ ኃይል የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ፣ ኢትዮጵያ 6ኛ፣ ሱዳን ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት መካከል ኬንያ ከአፍሪካ 12ኛ፣ ደቡብ ሱዳን 22ኛ፣ ሶማሊያ ደግሞ 34ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በግሎባል ፋየር ፓወር የአገራት ወታደራዊ ጥንካሬ የደረጃ ዝርዝር ውስጥ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት የተካተቱት 35 ብቻ ናቸው። በዚህም ምክንያት በወታደራዊ የጥንካሬ አመላካች የደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ 19 የአፍሪካ አገራት ያልተካተቱ ሲሆን የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ኤርትራና ጂቡቲ በዚህ ውስጥ ካልገቡት መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ፣ በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ስር የሠላም ማስከበር ተልዕኮን ተቀብሎ በመሰማራት ከሌሎች የአህጉሪቱ አገራት የበለጠ ሚና እንዳለው የሚነገር ሲሆን፤ ለተባበሩት መንግሥታት የሠላም ማስከበር ስራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን በማቅረብ ቀዳሚ መሆኑ ይጠቀሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ሠራዊት አደረጃጀት ላይ ለውጦች እየተደረጉ መሆናቸው፣ እንዲሁም ሠራዊቱን በሥልጠናና በትጥቅ የማዘመን ሥራ እተካሄደ መሆኑ መገለጹ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment