የወጣቶች እና የአፍላ ወጣቶች ጤናን መጠበቅ የሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነት ነው
___________________
የጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶች እና የወጣቶችን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ነው የተባለለትን የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ ባደረገበት ስነስርአት ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ሀላፊ እና ከፍተኛ አማካሪ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ዜጎቿ ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ የተለያዩ ስልቶችን ነድፋ እየሰራች እንዳለ አስታውሰው የወጣቶች እና የአፍላ ወጣቶችን ጤና ትኩረት እንዲያገኝ እና አምራች እና ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ የአምስት አመት ስትራቴጅክ እቅድ ማዘጋጀት እና ወደ ስራ ማስገባት መሆኑን ተናግረዋል። ስትራቴጂክ እቅዱ ተግባራዊ እንዲደረግ እና የወጣቶች እና የአፍላ ወጣቶች ጤና እንዲጠበቅ ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያወሱት አቶ ፍቃዱ ሁሉም ባለድርሻዎች በትግበራ ሂደቱም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የሚኒስቴሩ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይራክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ሀገር ተረካቢ እና ዋነኞቹ የልማት ተዋናዮች እንደመሆናቸው የተሟላ ጤንነትና መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተው ለዚህም የጤና ሚነስቴር የወጣቶችን እና የአፍላ ወጣቶችን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችለው መዋቅርን በመፍጠር፣ በሰው ሀይል በማደራጀት እንዲሁም አጋር አካላትን በማቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የአፍላ ወጣቶች እና የወጣቶች ጤና ወጥነት ባለው እና አሳታፊ ሆኖ እንዲተገበርም የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክተሯ ሴክተሮች፣ አጋር አካላት እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በዝግጅቱ ማሳተፋቸውን፣ በቀጣይም ለትግበራው በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ስትራቴጅክ እቅዱም ይፋ በተደረገበት የጤና ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች፣ የሴክተር መስሪያቤት ተወካዮች እና አጋር አካላት በአካል እና በበይነ መረብ በሰነዱላይ ውይይት በማድረግ ተሳትፈዋል። ይፋ ከተደረገበት እለት ጀምሮም የአፍላ ወጣቶች እና የወጣቶች ጤና የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ ላይ እንደሚውል ታውቋል።
No comments:
Post a Comment