ዛሬ የምንመርቀው ቤተ መጻሕፍት ‹አብርሆት Enlightenment› ተብሎ ተሰይሟል። አብርሆት እውነትንና ዕውቀትን መሠረት በማድረግ ከድንቁርና ቀንበር ነጻ የመውጣት ሂደት ነው። እውነትን በአመክንዮ፣ በክርክር፣ በማስረጃ፣ በምርምር፣ የመፈለግ መንገድ ነው። ዕውቀት ወደ እውነት ለመድረስ ሁነኛው ጎዳና ነው ብሎ ያስባል። በአመክንዮ የሚመሠረት የሰው ልጆች ማኅበራዊ ኑሮ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ፣ መቻቻል ያለበት፣ ነጻነትን የሚያጎላና ለለውጥ ልብን ክፍት ያደረገ እንደሆነ ያምናል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ስለራሱ፣ ስለዓለምና ስለሌላውም ሁሉ የተሻለ ዕውቀት እንዲኖረው እና ማኅበራዊ ሕይወቱን በአምክንዮ እንዲመራ ይተጋል።
ሰዎች በተመራመሩ፣ በተማሩና ባወቁ ቁጥር የተሻለ መቀራረብ ይፈጥራሉ ተብሎ ይታመናል። ድንቁርና ጨለማ ነው። በጨለማ ውስጥ ደግሞ ማወቅም መተዋወቅም አይኖርም። የሌለው ነገር ያለ፤ ያለውም ነገር የሌለ መስሎ ይታያል። የማናውቀውን ነገር እንፈራዋለን፤ እንጠላዋለንም። ስለማናውቀው ነገር የምንፈጥረው ሥዕል የተሳሳተ ነው። ለዚህ መድኃኒቱ ደግሞ ማወቅ ነው። ማወቅ መተዋወቅን ያመጣል። የምናውቀውን ነገር እንቀርበዋለን። እናምነዋለን፤ እንዛመደዋለን፤ እንወደዋለን፤ አብረነው ለመኖር ፈቃደኞች እንሆናለን።
የለውጡ ጉዞ ከተጀመረ ጊዜ አንሥቶ ከታሰበባቸው ነገሮች አንዱ ዕውቀት መር የሆነ ማኅበረሰብ መመሥረት ነው። ማኅበረሰቡ ዕውቀትን ባገኘ ቁጥር ይበልጥ ይተዋወቃል፤ ይቀራረባል፤ ይተማመናል። አንዱ ስለሌላው የያዘውን የተሳሳተ ግምት በመተው በትክክለኛው ዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረዳትን ይይዛል። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ፤ ነባር ዕውቀቶችን ለሀገራዊ ልማት መጠቀም፤ ምርምሮችንና ጥናቶችን፤ ውይይቶችንና ክርክሮችን፤ ነጻ ሐሳብ መድረኮችን፤ ኪነ ጥበብን ማበረታታት፤ ደራስያንና የሐሳብ መሪዎችን ወደፊት ማምጣት፤ የለውጡ አንዱ መንገድ ሆኖ ቆይቷል።
በለውጡ ዘመን አርአያ ሆነው የተሠሩትን ሥራዎች ስናይ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው በተጨማሪ የአብርሆት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። የአንድነት ፓርክና የአድዋ ሙዝየም ታሪክን ለመጣያና ለመለያያ ሳይሆን ለመተዋወቂያና መተራረሚያ ለማድረግ የቆመ ነው። የመስቀል አደባባይ እድሳትና የሸገር ፓርክ ግንባታ ሃይማኖት፣ ባህልና ኪነ ጥበብ ለሚያመጡት አብርሆት በር የከፈተ ነው። የእንጦጦ የሥዕል ጋለሪ አብርሆትን ከሚያስገኙት ረቂቅ ጥበቦች ለሁለቱ ለሙዚቃና ሥዕል ዕድል የሰጠ ነው። መዝናኛ የሚመስሉት የእንጦጦ ፓርክ፣ የቸርቸር ጎዳናና ወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች አእምሮን ከተዋጊነትና ከግጭት አምራችነት ለማስፈታትና የሰከነ የሐሳብ መድረክን እንዲመርጥ ለማድረግ ታስበው የተሠሩ ናቸው። የጎርጎራ፣ የወንጪና የጨበራ ጩርጩራ ፕሮጀክቶች ለአንድ ዓላማ በሕዝቦች መካከል መገናኘትን፣ መተዋወቅን እና መደናነቅን ለመፍጠር ነው። የመለያየትን ግንብ አፍሮ የኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መስክ ለመፍጠር ነው።
ኢትዮጵያ የራሳቸውን ፊደል ቀርጸው፣ የራሳቸውን ትምህርት አደራጅተው፣ የራሳቸውን ታሪክ ከጻፉ ጥቂት የዓለም ሀገሮች አንዷ ናት። በእስልምናና ክርስትና ማዕከላት ብቻ ከ250ሺ በላይ በእጅ የተጻፉ መጻሕፍት በየገዳማቱና በየመስጊዶቹ ያሏት ሀገር ናት። በአፍሪካ የመጀመሪያውን ልቦለድ የጻፈች ሀገር ናት። ልጆቿ ዕውቀትን ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ፤ ሀገር አቋርጠውም ሲንከራተቱ የኖሩባት ሀገር ናት። ምንም እንኳን ሺ ዘመናትን የተሻገረ የሥነ ጽሑፍ ሥራና የትምህርት ተቋም ቢኖራትም፤ በመቶ ሺዎች የሚጠጉ መጻሕፍትን ብታመርትም፤ ዕውቀትን በማዕከል ይዘው ለዕውቀት ፈላጊዎች ተደራሽ የሚያደርጉ ማዕከላት ግን በብዛትና በብቃት የሏትም።
እስካሁን ከዩኒቨርሲቲዎች ውጭ ያለን ትልቁ ቤተ መጻሕፍት አንድ ነው። እርሱም በ1936 ዓም የዛሬ 78 ዓመት የተከፈተው ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ ቢያንስ በዞን ደረጃ አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ሊኖረን ይገባ ነበር። ግን አልሆነም። ይህ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ሲታሰብ አምስት አገልግሎቶችን እንዲያካትት ሆኖ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የተጻፉ መጻሕፍት እንዲገኙበት። አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የተሻለ የማንበቢያ ሥፍራ እንዲኖረው። ዲጂታል አገልግሎት መስጠት እንዲችል። በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ እንዲኖረውና በአካባቢው ያለውን የመናፈሻ ሥፍራ ለመጠቀም በሚያስችል ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ።
ከሥነ ሕንጻው ጀምሮ ዕውቀትንና ታሪክን እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ የተገነባ ነው። ‹አብርሆት ቤተ መጻሕፍት› የተባለውም ዋና ዓላማው እውነትና ዕውቀት ነጻ የሚያወጣውን ማኅበረሰብ ለመመሥረት ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያ ለልጆቿ የሥልጣኔን መንገድ መርጣለች። ለጠላቶቿ ደግሞ ክንደ ብርቱ ሆና ትጠብቃቸዋለች። የሥልጣኔው መንገድ ደግሞ መማር፣ መመራመር፣ መወያየት፣ መከራከር፣ በሐሳብ መሸናነፍ፣ ዕውቀትን ማነፍነፍ፣ በአመክንዮ፣ በማስረጃና በመረጃ ላይ መመሥረት ናቸው። በቀጣዩ ዘመን፣ መጀመሪያ ደረጃቸውን የጠበቁ ክልላዊ አብያተ መጻሕፍት እንዲኖሩን፤ በመቀጠልም ዞናዊና ወረዳዊ አብያተ መጻሕፍት እንዲኖሩን እንሠራለን። ኢትዮጵያ የምትገነባው በየደረጃው በሚደራጁ የዕውቀት ማዕከላት ውስጥ ነው።
ለዚህ ደግሞ ባለ አራት ማዕዘን ኅብረት ያስፈልገናል። መንግሥት፣ የአካባቢው ሕዝብ፣ በጎ አድራጊ አካላትና በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ። መንግሥት ቦታዎችን ያመቻቻል፤ አስተዳደሩን ይወስዳል። የአካባቢው ማኅበረሰብ የዐቅሙን አዋጥቶ ግንባታውን ያግዛል። በጎ አድራጊዎችም በግንባታው ላይ ይሳተፋሉ። በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ መጻሕፍቱን በማሰባሰብ፣ በቴክኖሎጂ የተሟላ እንዲሆን በማድረግና ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት አስተዋጽዖ ያደርጋል። እንደዚህ ከሆነ ዕውቀት እንደ ኢትዮጵያ ጅረቶች በየአካባቢው ይፈስሳል፤ ትውልድንም ያጠጣል። የነገዋ ኢትዮጵያ ከዛሬ በእጅጉ የተሻለች ትሆናለች፤ መሠረቷን እውቀት ያደረገች ሥልጡን ሀገር ትሆናለች።
ይህ ቤተ መጻሕፍት ሲታሰብ፣ ሲገነባና ሲሟላ አስተዋጽዖ ያደረጉትን ሁሉ በዚሁ አጋጣሚ ላመሰግን እወዳለሁ። ሕዝቡ ቤተ መጻሕፍቱን ተንከባክቦ፣ እንዳይበላሽ ጠብቆ፤ ሲጎዳ ጠግኖ፤ ሲጎድል አሟልቶ ለልጅ ልጅ በሚተርፍ መንገድ እንዲጠቀምበት አደራ እላለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታህሳስ 22፣ 2014 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment