ውክልና
Published
በቅድሚያ ወደ ድረ ገጻችን እንኳን ደህና መጣችሁ። ይህ ድረ ገጽ የተሠራው ከብዙ ዓመታት ልምድና በደንበኞቻችን አስተያየት ላይ በመመሥረት ስለሆነ፣ እባክዎ ጊዜዎን ወስደው የዚህን ድረ ገጽ ዋና ዓላማ በጥሞና ያንብቡት።
ውክልና ቀልድ አይደለም። በቅድሚያ አንድን ሰው ለመወከል ከመምረጥዎ በፊት፣ ለዚያ ተወካይ ለምንና ምን ዓይነት የውክልና ሥልጣን እንደሚሰጡት በጥሞና ያስቡበት። የውክልና ሥልጣን መስጠት ሳይሆን፣ የውክልና ሥልጣኑን ከተወካዩ ላይ **ማውረዱ** **ወይም** **መሻሩ** **በጣም** ከባድ ሂደት ነው።
ታዲያ እኛ ለደንበኞቻችን የውክልና ሥልጣን መስጫም ሆነ መሻሪያ ሰነድ በማዘጋጀት ያካበትነው ልምድ በጣም ብዙ ዓመታትን የፈጀ ልምድ ስለሆነ፣ በእኛ በኩል የተዘጋጀ የውክልና ማስረጃ ቅመም የሆነ፣ እርስዎን ከብዙ ውጣ ውረድ የሚያድን፣ በጣም የተዋጣለት ፍቱን መድኃኒት ነው።
ሥራችን አገር ቤት የራፖር ጸሐፊዎች ዓይነት፣ ወይም ገና ለገና የአማርኛ ታይፕ ማድረግ ስለቻሉ ብቻ፣ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ከሌላ ሰው አሮጌ ወይም ናሙና የውክልና ሥልጣን ገልብጠው፣ የአንዱን ከአንዱ አጋጭተው፣ ሌላ ጣጣ ውስጥ ሰውን የሚከቱ ዓይነት መናኛ ሥራ አይደለም።
ሥራችን በዓለም አቀፍ የጄኔቫና የሄግ ውሎች መሠረት ተመርኩዞ የሚሠራ ስለሆነ፣ ውክልናም ሆነ ሌሎች ሰነዶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ኢሚግሬሽን፣ አየር መንገዶች፣ ኤምባሲዎች፣ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ቀበሌዎች፣ ክፍለ ከተሞች፣ ክልሎች፣ አስተዳደሮች፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የጡረታ መምሪያ፣ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በመሬት አስተዳደርና በመሳሰሉት ቁልፍ ቦታዎች እንዲሠሩ ሆነው የረቀቁ ሰነዶች ናቸው።
ዓላማችን እርስዎ ያለዎትን ጉዳይ በወቅቱ እንዲያጠናቅቁ ነው። ይህ ማለት የውክልናውን ሰነድ የፈለጉበት ዋናው ዓላማ ግቡን እንዲመታ ነው።
አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ደንበኞች ከዕውቀት ማነስ የተነሣ፣ ውክልና ማዘጋጀት የወካይና የተወካይ አድራሻን ብቻ ቀይሮ፣ የሌላ ሰውን ውክልና ቃል በቃል መገልበጥ ብቻ ይመስላቸውና፣ መጠኑ ልቅ የሆነ ወይም ጎዶሎ የውክልና ሥልጣን ሰጥተው፣ የራሳቸውንም ሆነ የሰውን ጊዜ፣ ሕይወትና ገንዘብ ሲያባክኑ ማየት የተለመደ ነው።
ይህንን አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕዝብ ስናቀርብ፣ እስከዛሬ ለብዙ ዓመታት ያካበትነው የሥራ ልምድ ተጠቃሚዎች በካሊፎርኒያ ግዛት ብቻ ነዋሪዎች ስለነበሩ፣ ይህንን አገልግሎት ለሌሎችም ብንሰጥ ታላቅ ጥቅም ይኖረዋል ብለው ብዙ ደንበኞቻችን ስለነገሩን ነው።
ዛሬ ወገኖቻችን/ደንበኞቻችን በአራቱም የዓለም ማዕዘናት ተበትነው ስለሚገኙ፣ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ይህንን ዕድል ስንከፍት የመጀመሪያው ስንሆን፣ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት ዕድሉን ስናገኝ በጣም ደስተኞች ነን።
**ተጠንቀቁ።** ከልክ ያለፈ ወይም ውስን ውክልና ሰጥተው፣ በገንዘብዎ ወይም በንብረትዎ ላይ እንዳይፈርዱት። ይህን የምንለው እርስዎን ለማስፈራራት ሳይሆን፣ አስቀድሞ ለማስጠንቀቅ ነው።
የውክልና ሥልጣን ማስረጃ የሚሞላ ፎርም አይደለም። ነገር ግን፣ እንደየሁኔታው **የሚረቅ ሕጋዊ ሰነድ ነው።**
እኛ ጋር ውክልና ለማዘጋጀት ሲመጡ ወይም በስልክ ሲደውሉልን፣ መጀመሪያ ብዙ ቃለ መጠይቅ እናቀርብልዎታለን። ከዚያ እርስዎ በፈለጉት መሠረት፣ ያሰቡትን ተግባር የሚፈጽም፣ ቅምም የሆነ የውክልና ማስረጃ ሰነድ እናዘጋጃለን። ከዚያ የውክልና ሥልጣኑ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ እንዲሆን፣ ምን ምን እንደሚያስፈልግዎ ቅደም ተከተሉን እናስረዳዎታለን።
አሠራራችን ወይም ጠቅላላ ሂደቱ ትንሽ እረዘም ያለ ነው። ለዚህም በቂ ምክንያት አለን። ምክንያታችንም፣ “**ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል**” እንዳይሆን ነው። ታዲያ ችኮላ ጠላታችን ነው።
ከሁሉ ነገር ለእኛ የሚያስደስተን ነገር፣ በሥራችን ጉዳዩን ያስጨረሰ ደንበኛ ማየት ነው። ታዲያ እኛ ባዘጋጀነው የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ሰነድ ጉዳያቸውን ያስፈጸሙ ደንበኞቻችን በጣም ብዙ ናቸው።
ታላቁ ማወቅ ያለብዎት ቁም ነገር፣ የእርስዎ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ በግምት አይሠራም። ያ ማለት ደግሞ፣ የእርስዎን ሰነድ ልክ እንደ መለማመጃ አናደርገውም። ያለን የሥራ ልምድ ከ15 ዓመታት በላይ ሲሆን፣ በጣም ብዙ የውክልና ሰነዶችን ስለሠራን፣ ምን ለምን እንደሚጠቅም ጠንቅቀን እናውቃለን።
የእኛን ሥራ በመጠቀም ደንበኞቻችን ከፈጸሟቸው ጉዳዮች መካከል፣ ለምሳሌ ደንበኞቻችን፦
* ልጆቻቸውን ወደ አሜሪካ አስመጥተዋል።
* የውርስ መብት አስከብረዋል።
* ቤትና ንብረት ሸጠዋል/ገዝተዋል።
* የንግድ ድርጅት ሸጠዋል/ገዝተዋል።
* ሆስፒታል፣ ክሊኒክ ሠርተዋል።
* ቤት፣ የንግድ ድርጅት፣ መኪና፣ ማሽን አከራይተዋል።
* የጉዲፈቻ ውል ፈጽመዋል።
* የጋብቻ፣ የፍቺና የልደት የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
* ኮንዶ፣ መሬት፣ መኪና ተረክበዋል።
* ከባንክ ገንዘብ ማስወጣትም ሆነ ማስገባት ችለዋል።
* ከትምህርት ተቋማት የትምህርት ማስረጃ፣ ዲፕሎማም ሆነ ዲግሪ አውጥተዋል።
* ብድር ተበድረዋል፣ እንዲሁም ከፍለዋል።
* አክሲዮን ገዝተዋል፣ የአክሲዮን ድርሻ ተቀብለዋል።
* መብራት፣ ውሃ፣ የስልክ መስመር አስገብተዋል።
* ግብር ከፍለዋል።
ከዚህ በላይ ያሉት ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ እኛ እርስዎ በፈለጉት መንገድ ያሰቡትን ጉዳይ የሚያሳካ የውክልና ሥልጣን እናዘጋጃለን።
ዋናውና ትልቁ ሂደት ደግሞ፣ የሚዘጋጀው የውክልና ሥልጣን ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ ያ ውክልና በኢትዮጵያም ሆነ በማንኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይነት እንዲኖረው የሚደረገው ሂደት ነው።
ይህ ሂደት፣ እርስዎ እንዳለዎት የዜግነትና የመኖሪያ ፈቃድ ሁኔታ፣ የሚወስደው ጊዜ ሊያጥርም ሆነ ሊረዝም ይችላል። ይህ ማለት፣ ለምሳሌ፣ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ ሰውና ቀኑ ያልተቃጠለ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ውክልናውን ለማጠናቀቅ የሚወስድባቸው ጊዜ በጣም ይለያያል።
Comments