ጋብቻ በሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጠር የግል እና የቤተሰብ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በሕግ የተደነገገ መብትና ግዴታንም ጭምር የሚፈጥር ተቋም ነው።
ከዘህ አንፃር በዋናነት የሚጠቀሰው ለትዳር ጓደኛ ታማኝ የመሆን ግዴታ ሲሆን፣ የጋብቻ ታማኝነትን የሚጎዱ ድርጊቶችን ሕጉ እንደ ወንጀል ይመለከታል።
በዚህ መነሻነትም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 652 አመንዝራነት በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ ደንግጓል። ይህ ጽሑፍም የዚህን ወንጀል ምንነትና ተጠያቂነት በአጭሩ ይዳስሳል።
የወንጀሉ ምንነት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 652(1) መሠረት አመንዝራነት ማለት በፍትሐብሔር ሕግ የታወቀ የፀና የጋብቻ ማለትም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሃይማኖት ወይም በባህል ሥርዓት የተፈፀመ ጋብቻ ግንኙነት ውስጥ ያለ ሰው ከትዳር አጋሩ ውጪ ከሆነ ከሌላ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ነው፡፡ በተመሳሳይ ሕጋዊ ጋብቻ እንዳለው እያወቀ በጋብቻ ውስጥ ካለ ሰው ጋር ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈፅም ሰውም የሚጠየቅ ይሆናል፡፡
በግል አቤቱታ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 652 ከሌሎች አንዳንድ የወንጀል ድንጋጌዎች የሚለየው የተጎጂው የትዳር አጋር ቅሬታ ወይም አቤቱታ እንደ መነሻ ሁኔታ መጠየቁ ነው። ድንጋጌው በተበደለው ባለትዳር የግል አቤቱታ፣ “upon complaint by the injured spouse” የሚለውን መስፈርት በግልጽ ያስቀምጣል። በመሆኑም ተበዳዩ አቤቱታ ካላቀረበ በቀር ፖሊስ በራሱ ተነሳሽነት ምርመራ ማድረግም ሆነ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመሥረት እንደማይችል ሕጉ ይደነግጋል። ይህ ማለት የአመንዝራነት ጉዳይ በተጎጂው የትዳር አጋር ፈቃድና ቅሬታ ላይ የተመሠረተ የክስ አጀማመር መስፈርት እንዳለው የሚያሳይ በመሆኑ የግለሰቦችን የግላዊ ነፃነት ጥበቃ የሚያደርግ ድንጋጌ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
አመንዝራነት የሚያስከትለው ቅጣት ከላይ የተመለከተው የአመንዝራነት ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ እና በተጎጂው የትዳር አጋር ቅሬታ ወይም የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እስራት (ከ10 ቀናት እስከ 3 ዓመት)ወይም በመቀጮ የሚቀጣ ይሆናል። የተበዳይ ድርጊት የሚኖረው የሕግ ውጤት አንቀጽ 652(1) እንደተጠቀሰው የትዳር አጋሩን እንዲያመነዝር ያነሳሳው ወይም የገፋፋው አቤት ባይ ከሆነ ወይም ለተፈፀመው ድርጊት ይቅርታ ካደረገ ወይ ከድርጊቱ ጥቅም ካገኘ ወንጀል ፈፃሚው ተጠያቂ እንደማይሆን ሕጉ ይደነግጋል። ይህም ድንጋጌው የተጎጂው ፈቃድና አመለካከት የሚኖረውን ሚና የሚያሳይ ሲሆን የእነዚህ ሁኔታዎች መኖር በማስረጃ እና በፍርድ ሂደት መረጋገጥ ይኖርበታል።
ተጋቢዎች አብረው መኖር ካቆሙ የሚኖረው የቅጣት ልዩነት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 652(2) ስር እንደተደነገገው የአመንዝራነት ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ባልና ሚስቱ ቀደም ብለው በመካላቸው በተፈጠረ ጠብ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ አብሮ መኖር አቁመው በነበረበት ጊዜ ከሆነ ፍርድ ቤት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 180 መሠረት ቅጣቱን ሊያቀል ይችላል።
ይህ የሚያሳየው ሕጉ የወንጀሉን ተሳታፊ አካላት ብቻ ሳይሆን የድርጊቱን ተጨባጭ ሁኔታም ከቅጣት አንፃር እንዲመዘን ለፍርድ ቤት ሥልጣን መስጠቱን ነው። በትዳር ቤት ውስጥ ውሽማ ማስገባት ሌላው በአንቀጽ 652(3) እንደተደነገገው ጥፋተኛው የትዳር አጋሩን ሳይፈታ ወይም ሌላው ተጋቢ ጥሎት ሳይሄድ ውሽማ መኖሪያ ቤቱ ያስቀመጠ እንደሆነ ቅጣቱ ከ3 ወር በማያንስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ነው። ማጠቃለያ ትዳር የቤተሰብ መሠረት በመሆኑ በሕጋዊ የትዳር ግንኙነት የተጣመረ ሰው ከትዳር አጋሩ ውጪ የግብረስጋ ግንኙነት ከፈፀመ በወንጀል ሕጉ በተመለከተው መሠረት በወንጀል ተጠያቂ የሚሆን በመሆኑ ማንኛውም ባለትዳር ለትዳሩ ታማኝ በመሆን ቤተሰቡን ከፍቺና ከማኅበራዊ ቀውስ ሊጠብቅና ራሱንም ከወንጀል ተጠያቂነትም ሊያድን ይገባል፡፡ በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Comments