Shop Amazon

Saturday, January 17, 2015

ግለሰቡ በኢቦላ ቫይረስ አለመሞቱ በድጋሚ በመረጋገጡ አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ መሰጠቱ ተገለጸ





ግለሰቡ በኢቦላ ቫይረስ አለመሞቱ በድጋሚ በመረጋገጡ አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ መሰጠቱ ተገለጸ
--------------------
በግል የሥራ ጉዳይ ወደ ሴራሊዮን አቅንቶ የነበረዉና ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ወዲህ ጠንካራ ክትትል ሲደረግበት የቆየዉ ግለሰብ ህይወቱ ያለፈዉ በኢቦላ ቫይረስ አለመሆኑ በመረጋገጡ አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ መሰጠቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የኢቦላ መከላከል ግብረ ሀይል አባላት የሆኑት ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ባለፈዉ ረቡእ ንጋት ላይ ህይወቱ በጭንቅላት ወባ እንዳለፈ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለ የምርመራ ላብራቶሪ ተረጋግጧል፡፡ ለኢቦላም በሃገር ዉስጥ በተደረገዉ ምርመራ ከኢቦላ ነፃ እንደሆነ ቢራገጥም ግለሰቡ የመጣዉ በኢቦለ ከተጠቁት አገሮች አንዷ ከሆነችዉ ሴራሊዮን በመሆኑ ለድጋሚ የማረጋገጫ ምርመራ የደም ናሙናዉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ በኢቦላ ቫይረስ የተጠቃ አለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኤንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዳዲ ጂማ እና በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር መርዓዊ አራጋዊ በጋራ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ኢቦላን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነች ሲሆን በተለይ የቫይረሱን ምንነት ለማረጋገጥ ያቋቋመችዉ ላብራቶሪ እና የባለሙያዎቹን ብቃት በግለሰቡ ላይ በተደረገዉ ምርመራ ማረጋገጥ መቻሉ እንደ ጠንካራ ጎን እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡


ቀደም ሲል ለድጋሚ ማረጋገጥ የግለሰቡ የደም ናሙና ወደ አሜሪካ እንደሚላክ የተገለፀ ቢሆንም አሜሪካ ለመድረስ እና ዉጤቱን ለማግኘት ከ2 ሳምንት በላይ ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ የምርመራ ዉጤቱ እስኪታወቅ ከግለሰቡ ጋር ግንኙነትና ንክኪ የነበራቸዉ ሰዎችን አግልሎ ማቆየቱ ብዙ ጊዜ እንዳይፈጅ በማሰብ በአጭር ጊዜ ዉጤቱ ሊገለጽ ወደተቻለበት ደቡብ አፍሪካ መላኩንና ዉጤቱም በፍጥነት እንዲታወቅ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ እስከ ዋሽንግተን ከዚያም እስከ አትላንታ ናሙናዉን ለማድረስ ከ20 ሰዓት በላይ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶ/ር መርዓዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ በአጭር ጊዜ ዉጤቱ በመታወቁ ከአካባቢያቸዉ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዉ የነበሩት ከተጠርጣሪዉ ጋር ንክኪ የነበራቸዉ ሰዎች ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉና ወደ መደበኛ ተግባራቸዉ እንዲገቡ የተጠርጣሪዉ አስከሬንም ለቤተሰቦቹ መስጠት አስችሏል ብለዋል፡፡
ተጠርጣሪዉ ግለሰብ የአካባቢ ጤና ስፔሻሊስት /ባለሙያ/ የነበረና በራሱ የግል ጥረት በአንድ የዉጪ ድርጅት ተቀጥሮ ወደ ሴራሊዮን ሄዶ ሲሰራ የቆየ እንደነበር ያስታዉሱት ዶ/ር ዳዲ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላም ከቦሌ አየር ማረፊያ ጀምሮ ጠንካራ ክትትል ሲደረግበት እንደቆየ ገልፀዋል፡፡
የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በግለሰቡ ሞት ምክንያት የተሰማዉን ሀዘን ለቤተሰቦቹ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩነኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ ኢማኖ በትናንትናዉ ዕለትም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች በንክኪ ምክንያት በተገለሉ ቤተሰቦች አካባቢ ተገኝተዉ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ የተደረጉበትን ምክንያት በመግለጽ ዉጤቱ ከኢቦላ ነፃ ቢሆንም ተጨማሪ ማረጋገጫዉ እንደደረሰ የሚለቀቁ እንደሆነ ገልጸዉ ማፅናናታቸዉንና ማረጋጋታቸዉን በጋዜጣዊ መግለጫዉ ወቅት ገልፀዋል፡፡
Source:
Federal Ministry of Health,Ethiopia

No comments:

Post a Comment