Shop Amazon

Thursday, April 2, 2015

የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕገወጥ ላላቸው ነዋሪዎች ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሊሰጥ ነው

የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕገወጥ ላላቸው ነዋሪዎች ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሊሰጥ ነው
- ሳይፈቀድላቸው መሬት የያዙ 46,042 ባለይዞታዎች ተመዝግበዋል
- በኮንዶሚኒየም ፕሮግራሞች (10/90፣ 20/80 እና 40/60) ዕድሎች ተጠቃሚ አይሆኑም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገወጥ መንገድ የመሬት ባለቤት ሆነዋል ላላቸው ነዋሪዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠት ሕጋዊ ሊያደርጋቸው ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. ባሉት ዘጠኝ ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዕውቅና ውጪ ባለይዞታ የሆኑ ነዋሪዎች ናቸው ሕጋዊ እንዲሆኑ የተወሰነላቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው ‹‹ሕገወጦችን ሕጋዊ የማድረግ ሒደት›› የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ምክንያት የሆነው፣ ከጥቂት ወራት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባፀደቀው መመርያ ነው፡፡ መመርያውን ተግባራዊ ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ባለሙያዎች እየተዘጋጁ መሆኑ ታውቋል፡፡
‹‹አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎችን ለማስተካከልና ለመከላከል›› በሚል ርዕስ የወጣው የአፈጻጸም መመርያ ከመጋቢት 1988 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 1997 ዓ.ም. ድረስ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎች ሕጋዊ ይሆናሉ ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ተፈጻሚ የሚሆኑት በሦስት መንገድ የተያዙ ይዞታዎች ናቸው፡፡ የመጀመርያው አግባብ ካለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ የከተማ ቦታዎች፣ ሁለተኛው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በማስፋፊያ የተያዙ ይዞታዎች፣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ በአርሶ አደሮች ለመኖሪያ አገልግሎት የተያዙ ቦታዎች ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሰሞኑን ለምክር ቤት ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድላቸው መሬት የያዙ 46,042 ባለይዞታዎች ተመዝግበዋል፡፡ ‹‹በአሠራሩ መሠረት እየተጠራ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፤›› በማለት ከንቲባው በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ የከተማ ልማትና የመሬት ማደስ ኤጀንሲ ምንጮች እንደገለጹት፣ ለእነዚህ ባለይዞታዎች ካርታ ለመስጠት የሚያስችል የማጣራት ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በሕገወጥ መንገድ የያዙ ባለይዞታዎችን ሕጋዊ የማድረግ ሐሳብ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ ሒደቱን የሚቃወሙ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ይህ አሠራር ሕጋዊ ነዋሪዎችን ወደ ሕገወጥ ተግባር የሚገፋፋና አድሏዊ ነው፡፡ እነዚህ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ የከተማው አስተዳደር ውሳኔ ሕጋዊ የሆኑትን ነዋሪዎች የማያበረታታና በአንፃሩ ሕገወጥነትን የሚደግፍ ነው የሚል ነው፡፡
ይህንን የባሙያዎች አስተሳሰብ ግን መመርያው አይቀበለውም፡፡ ቀደም ሲል ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌም ከዚህ ሐሳብ ጋር እንደማይስማሙ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ መመርያው እንደሚለው ሕገወጦችን ሕጋዊ የማድረግ ሒደቱ በከተማው የተንሰራፋውን ሕወገጥ የመሬት ይዞታና ግንባታን ከመሠረቱ ይገታል፡፡ ከአድሏዊ አሠራርና ከሙስና የፀዳ፣ ሕግን የተከተለ፣ የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም ነው ብለዋል፡፡ ሕገወጦችን ሕጋዊ የማድረግ ሒደት ምናልባት ከዚህ ቀደም መሬት ላልወረሰው ሰው የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ለአቶ መኩሪያ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
አቶ መኩሪያ ሲያብራሩም፣ ‹‹በሕገወጥ መንገድ መሬት የያዙ ሰዎች ይዞታውን በነፃ አያገኙም፡፡ ከፍለው ነው የሚያገኙት፡፡ ሁለተኛው በቀጥታ ወደ ሊዝ ሥርዓት ይገባሉ፡፡ ሦስተኛ የኪራይ ድልድል ባልናቸው ዕድሎች ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ማለትም በኮንዶሚኒየም ፕሮግራሞች (10/90፣ 20/80 እና 40/60) ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡››
‹‹ስለዚህ ከኅብረተሰብ ሞራልና ከማኅበረሰቡ እሴት አንፃር ሕገወጥነት ትክክል አይደለም፡፡ በገንዘብም ተቀጥተው ነው ይህንን መሬት የሚያገኙት፤›› በማለት አቶ መኩሪያ አስረድተዋል፡፡ ተጻፈ በ ውድነህ ዘነበ Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment