"የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር በአሸባሪው የጥፋት ቡድን የወደሙና የተዘረፉ የጤና ተቋማትን መልሶ በማደራጀት በፍጥነት ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ከማድረግ አንጻር ተምሳሌት የሚሆን ድጋፍ በማድረግ እየሰራ ይገኛል" ክቡር አቶ አወል አርባ - የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት
____________________
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በአፋር ክልል በአሸባሪው የጥፋት ቡድን ለወደሙ የጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውሉ ግምታቸው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና መገልገያ መሰሪያዎችና ቁሳቁሶችን በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት ጤና ሚኒስቴር በአሸባሪው የጥፋት ቡድን የወደሙና የተዘረፉ የጤና ተቋማትን መልሶ በማደራጀት በፍጥነት ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ከማድረግ አንጻር ተምሳሌት የሚሆን ድጋፍ በማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ በካሄደው ወረራ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን የደረሰውን አደጋ በመቋቋም አሸባሪውን የጥፋት ቡድን መደምሰስ መቻሉን ገልጸዋል። በክልሉ የደረሰውን አደጋም ለመቀልበስና የወደሙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት መላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከጎናቸው በመቆም እያደረጉ ያለውን ርብርብ ያደነቁት ፕሬዚዳንት አወል የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየውን ፍቅር በደንብ ማየት የተቻለበት ጊዜና አጋጣምም መሆኑን ተናግረዋል። ጤና ሚኒስቴርና ስርት የተባለ የግብረሰናይ ድርጅት በክልሉ ለወደሙ የጤና ተቋማት አገልግሎት ላበረከቱት ድጋፍ በክልሉ ህዝብና መንግስት እንዲሁም በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው አሸባሪውን የጥፋት ኃይል በመደምሰስ የክልሉ መንግስትና ህዝብ የፈጸመውን አኩሪ ገድልና ጀግነት መለው የኢትዮጵያ ህዝብ የኮራበት መሆኑን አንስቶ በክልሉ የወደሙና የተዘረፉ ጤና ተቋማትን በተቻለ መጠን በፊት ከነበሩበት በተሻለ መልኩ ጭምር ወደስራ እንዲገቡ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው በአሸባሪው የጥፋት ቡድን በክልሉ ከውደሙት አንዱ የሆነው የጭፍራ ጤና ጣቢያ በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ ተደርጎለት በፊት ከነበረበት በተሻለ መልኩ ከፍ በማድረግ በመጀመሪያ ሆስፒታል ደረጃ በቅርቡ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል።
በተጨማሪም የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ከአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታልን የስሬ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን የሆስፒታሉ አመራሮችና ባለሙያዎች የሆስፒታሉ መደበኛ ስራ ሳይስተጓጎል በግዳጅ ላይ ለቆሰሉ የጀግናው መከላከያ ሰራዊት አባላት እያደረጉ ያሉትን ህክምና እና እንክብካቤ እጅግ የምያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እያስገነባ ያለው የላቦራቶሪ ማዕከል ግንባታ በተቻለ ፍጥነት ቶሎ አልቆ ስራ እንዴጀምር ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የስርት (Center for international reproductive health training- CIRHT) ማኔጅንግ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጤና ሚኒስቴር አስባባሪነት ድርጅታቸው ከዚህ ቀደምም በአማራ ክልል በጦርነቱ ለወደሙ የጤና ተቋማት ድጋፍ ያደረገ መሆኑን አስታውሰው በዛሬው ዕለትም በአፋር ክልል የወደሙና የተዘረፉ ጤና ተቋማትን ወደነበረበት መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያግዙ የተለያዩ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እንዲሁም 100 ሜድካል አልጋዎች ከነፍራሽ ጋር መበርከቱን ገልጸዋል ። ለወደፍትም ድርጅታቸው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
No comments:
Post a Comment