Shop Amazon

Thursday, November 17, 2022

የአዲስ አበባ ድምቀት ሆኖ ለ20 ዓመታት የዘለቀው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ”

የአዲስ አበባ ድምቀት ሆኖ ለ20 ዓመታት የዘለቀው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” 
*****************
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአዲስ አበበ መለያ እስከመሆን የደረሰ እና በየዓመቱ  በጉጉት የሚጠበቅ ውድድር እስከመሆን ደርሷል። በአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ከ1994 ዓ.ም ተጀምሮ ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀው የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ታላቅ የጎዳና ላይ የብዙኃን ትርኢት ስምና ዝና አትርፎ በዓለም ላይ ካሉት ውድድሮች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች ከ100 በላይ ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ ለማድረግ ችሏል።

የሩጫ ውድድር የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ መድረኮችም ጭምር የሚያስጠራ እና ሰንደቅ አላማዋም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የሚያደርገው የስፖርት ዓይነት እንደሆነ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ሁነቶች አንዱ የሆነው እና በናፍቆት የሚጠበቀው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ሲካሄድ በቆየባቸው 20 ዓመታት በተሳታፊዎች መካከል ደማቅ ወዳጅነት እንዲመሰረት በማድረግ የመዲናዋ አንዱ የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

40 ሺህ የሚደርሱ ብዝሃ ስብጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ያሉት ውድድሩ ሁሉም በአንድነት፣ በደስታ፣ በተለያዩ መርሆዎች በስኬት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል።  

ውድድሮቹ በ8 ዓይነት ዘርፍ የሚካሄዱ ሲሆን፣ የተሳታፊዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአንድ ጊዜ እስከ 40 ሺህ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ የቻለ ታላቅ አገራዊ ትእይንት ለመሆን በቅቷል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኃላ.የተ.የግ.ማ ቋሚ ሰራተኞቹ እና አዘጋጅ ቡድኖቹ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተደራጀ ሲሆን ከተለያዩ አጋሮቹ ጋር በመሆን የውድድር እና ተያይዞም አጋሮቹን የማስተዋወቅ ዘመቻዎች ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከአገር ውስጥም አልፎ በጋና የሚሊኒየም ማራቶን እና በደቡብ ሱዳን ጁባ ታላቁ የደቡብ ሱዳን ሩጫን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ውድድሮች ላይ የማማከር ሚና ወስዶ ሲሰራ ቆይቷል።

“ሩጫን ለሁሉም ሰው የአኗኗር ዘይቤ ማድረግ!” የሚለውን እንደ ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ድርጅቱ፣ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የጅምላ ተሳትፎ ውድድሮችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ገጽታ ማሳደግ፣ ጤናማ ኑሮና ጠቃሚ ማህበራዊ መልዕክቶችን ማስተዋወቅ እና ለወጣት አትሌቶች የመወዳደሪያ መድረክ በመፍጠር የዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉበትን ዕድል የመፍጠር ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በዚህም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ11 ጊዜ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር በውቧ ሐዋሳ ከተማ ያካሄደ ሲሆን “ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪ.ሜ” ውድድር ደግሞ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለ19 ጊዜ ከ100 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከ5 እስከ 75 የሚሆኑ ሴቶችን ያሳተፈ ውድድር አድርጓል።

በተጨማሪም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ “የእንጦጦ ፓርክ ፕሬዲተር ሩጫ” በሚል 700 ሰዎች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ውብ በሆነው የእንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ ውስጥ በየወሩ ያከናውናል።

ሌላው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚታወቀው በየአመቱ በሚያካሂደው “የፕሌይማተርስ የልጆች ሩጫ ውድድር” ነው። ይህ ውድድር እስካሁን ለ14 ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የ15ኛው ውድድር ህዳር 10፣ 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ2015 ዓ.ም ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ ውድድሩን የፊታችን እሁድ ህዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም  ይካሄደል፤ይህን የሁለት አስርት ዓመታት ዕድሜ ያለውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ከጥንስሱ ጀምሮ በቀጥታ ስርጭት ወደ ታዳሚያኑ ሲያስተላልፍ የነበረው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን  የፊታችን እሁድም ሰፊ ሽፋን ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

No comments:

Post a Comment