Shop Amazon

Thursday, April 4, 2024

ሽግግር ወደ ኤሌክትሪክ ትራንስፖርት!

 ሽግግር ወደ ኤሌክትሪክ ትራንስፖርት!

በርካታ የአለማችን ሀገራት ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሽግግር ለማድረግ አስበው እቅድ አውጥተዋል፣ በዚህ ደግሞ የስካንዲኔቭያን ሀገራት ቅድሚያውን ይይዛሉ።

እኛ ሀገር ደግሞ ከሰሞኑ የኤሌክትሪክ መኪና፣ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል... ወዘተ በአስገዳጅነት እየተተገበረ ነው ወይም ሊተገበር ታስቧል።

የእኛ ሀገር 'ዋና አላማ' የተመናመነውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሆነ ሲታመን ሌሎች በተለይ ያደጉ እና እንደ ህንድ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ደግሞ የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ ነው።

እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ይህን ቀስ በቀስ ለመተግበር እቅድ ይዘዋል፣ እኛ ሀገር ደግሞ በአስቸኳይ አሁኑኑ ይተግበር ተብሏል። ሌላው ቀርቶ የኤሌክትሪክ መኪና ብቻ ይግባ የሚለው ህግ እጅግ በአስቸኳይ አሁኑኑ ይሁን ከመባሉ የተነሳ እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር ያሉ አካላት መረጃው እንኳን አልነበራቸውም።

በዚህ ፅሁፍ ላነሳ ያሰብኩት ወደ ኤሌክትሪክ የሚደረገው አስቸኳይ ሽግግር ሊያጋጥሙት የሚችሉትን ተግዳሮቶችን እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ነው።

1. የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ የማድረጊያ ጣብያዎች በስፋት ያስፈልጋሉ፣ ይህ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አንፃር ችግር ሊሆን ቢችልም አንዱ ዋና ጉዳይ ነው፣

2. የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በስፋት ባለበት ሀገር ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ የሚደረግ ሽግግር በርካታ ተሽከርካሪዎችን መብራት በጠፋ ቁጥር ከጥቅም ውጪ ሊያደርግ ይችላል፣

3. ይህ ሽግግር በነዳጅ ማጓጓዝ እና ማከፋፈል እንዲሁም ትንሽም ቢሆኑ የነዳጅ መኪና አምራች ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ግለሰቦችን ከስራ ውጪ ያረጋል፣ ስለዚህ ካሁኑ እነዚህን ዜጎች በሽግግሩ ሂደት ውስጥ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፣

4. ሌላው አለም ካሁኑ እየተቸገረ ያለበት ጉዳይ ደግሞ አገልግሎት የጨረሱ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች ጉዳይ ነው።  እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ይህ ከፍተኛ እና መርዛማ ብክለት እያስከተለባቸው ስለሆነ የህግ ማእቀፎችን አዘጋጅተዋል፣ ይህ በኢትዮጵያም ሊታሰብበት ይገባል፣

5. የኤሌክትሪክ መኪናዎች የመጓዝ አቅም ከግዜ ወደ ግዜ እየተሻሻለ ቢሆንም በነዳጅ ከሚሰሩት አንፃር ሲታይ በአንድ ቻርጅ መጓዝ የሚችሉት ርቀት በተለይ ወደ ክፍላተ ሀገራት የሚደረጉ ረጃጅም ጉዞዎች ላይ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።

6. በነዳጅ የሚሰሩ ሞተር ሳይክሎች በአስቸኳይ ወደ ኤሌክትሪክ ሞተር ይቀይሩ ተብሏል፣ ይህን ከፍተኛ ወጪ መንግስት የሚጋራው ስላላሆነ በሞተር ስራ ላይ ለሚገኙ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል፣

ሲሆን ሲሆን በአመታት ወይም በወራት ሂደት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማስወጣት (phase out ማድረግ) የተሻለው እንደሆነ በአለም ዙርያ ያሉ ተሞክሮዎች ያሳያሉ።

ካለ ምንም ሽግግር "ከዛሬ ጀምሮ" ተብለው የተተገበሩ እነዚህ ውሳኔዎች እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮች በማሰብ ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ፣ ኢንቨስትመንት እና ትብብር ከሌለ ውጤቱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

Via:EliasMeseret

No comments:

Post a Comment