Saturday, March 14, 2026
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ ጥቆማዎች: ከመንግስት የፋይናንስ ጥገኝነት እስከ ተጫዋቾች ደሞዝ ቀውስ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ ጥቆማዎች: ከመንግስት የፋይናንስ ጥገኝነት እስከ ተጫዋቾች ደሞዝ ቀውስ
Meseret Media
Mar 14
በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ ለመሠረት ሚድያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስን መሰረታዊ ማነቆዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች የምንፈትሽበትን ይህንን ተከታታይ የጥናት ፅሁፍ በትኩረት እየተከታተላችሁ ስለሆነ ከልብ እናመሰግናለን።
በክፍል አንድ ጽሁፍ የክለቦቻችንን የመንግስታት የፋይናንስ ጥገኝነት፣ የመንግስት እጅ ያለበትን የአመራር አደረጃጀት እና ደካማ ተቋማዊ ቁመና መዳሰሳችን አይዘነጋም። ባለፈው በቀረበው የክፍል ሁለት ጽሁፍ ደግሞ፣ ወደ ክለቦቹ የውስጥ አሰራር በማተኮር ሶስት ወሳኝ ችግሮችን ተመልክተናል፣ እኝህም፦ በሰለጠነ የሰው ሃይል አለመመራታቸው፣ በክለቦች ውስጥ በጉልህ የሚታየው የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት መጥፋት፣ እንዲሁም የስፖርቱን እድገት የሚፈታተነው የበጀት ዕቅድ እና አጠቃቀም ጉድለት ነበሩ።
እነዚህ እስካሁን የተመለከትናቸው ስድስት አንኳር ነጥቦች፣ የእግር ኳሳችንን የችግር ስረ-መሰረት በተወሰነ መጠን አሳይተውናል። በዛሬው የክፍል ሦስት ተከታታይ ፅሁፍ፣ የክለቦቻችንን ዕጣ ፈንታ እየወሰኑ ያሉ ተጨማሪ ተግዳሮቶች ተዳሰዋል። እስካሁን ስድስት መሰረታዊ ችግሮችን በዝርዝር የዳሰስን በመሆኑ፣ የዛሬውን ትንታኔያችንን የምንጀምረው በጥናቱ ከተለዩት ማነቆዎች መካከል ሰባተኛው ከሆነው (የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር) ተግዳሮት በመነሳት ይሆናል።
የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር
የተጫዋቾች የክፍያ አስተዳደር፣ ከበጀት ዕቅድ እና አጠቃቀም ጉድለት ጋር በተሳሰረ፣ በጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት እና በተደጋጋሚ የተነሳ የሊጉ ፈታኝ ነባራዊ ሁኔታ መሆኑ ተገልጿል። የተጫዋቾች ክፍያ፣ ክለቦች ከሚመድቡት በጀት የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ቢሆንም፣ የአገሪቷ እግር ኳስ ከደረሰበት ደረጃ ጋር ሲነጻጸር ወጪው እና በብሔራዊ ደረጃ ያለው ውጤት መካከል ከፍተኛ ክፍተት መታየቱ ጉዳዩ ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ነው።
የተጫዋቾች ደሞዝ ድርድር፣ የተጫዋቾች ደሞዝ አከፋፈል፣ የተጫዋቾች ዝውውር፣ የፊርማ ክፍያ፣ የማበረታቻ ክፍያ፣ ወዘተ በአግባቡ የሚተገበርበት መመሪያ አለመኖሩ እና የአሰራር ስርዓት አለመዘርጋቱ በዘልማዳዊ አሰራር ክፍያዎች እንደሚስተናገዱ የጥናቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ክለቦች፣ በየአመቱ ያላቸውን በጀት አስቀድሞ ማወቅ፣ ምን ያህል ተጫዋች ማምጣት እንዳለባቸው መተንበይ፣ እንዲሁም ተጫዋቾችን ሲቀጥሩ በምን አይነት መንገድ እንደሚያተርፏቸው፣ በምን ያህል መንገድ ክለቦቻቸውን እንደሚታደጓቸው፣ እና ሌሎች ተመሳሳይ በጥንቃቄ መያዝ ያለባቸው ጉዳዮችን በአግባቡ ሳይስተናገዱ እንደሚሰራ የጥናቱ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ጠቁመዋል። አብዛኞቹ ተሳታፊዎች፣ የተጨዋቾች ክፍያ የክለቦችን እውነተኛ አቅም ያላመጣጠነ ፣ ወጥ ያልሆነ የገበያ ዋጋ የሚታይበት፣ እና ከሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ያልተጣጣመ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። በመሆኑም፣ የአገራችንን እግር ኳስ እየበረዙ ካሉ ነባራዊ ሁኔታዎች መካከል የተጫዋቾች ደሞዝ አስተዳደር ቅድሚያ ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ሆኖ ተነስቷል። ብዙዎች የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ተጫዋቾች ጥሩ ክፍያ ሊያገኙ ይገባል የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን፣ ስጋታቸው በመሰረተ ልማቱ እና በደሞዝ ክፍያው መጠን መካካል ሚዛኑን ያልጠበቀ አካሄድ መኖሩ እንደሆነ እይታቸውን አጋርተዋል። በተለይም፣ የተደራጀ እንደ ቢሮ፣ ባለሞያ፣ እና ድርጅታዊ መዋቅር ሳይኖራቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለተጫዋች የመክፈሉ ባህል ብዙዎቹ ተሳታፊዎችን ግር ያሰኘ አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።
የተጫዋቾች ደሞዝ መናር ጀርባ የተሳሰሩ ነባራዊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተሳታፊዎች ያነሱ ሲሆን በተደጋጋሚ ከተነሱት ነጥቦች መካከል፦ ክለቦች ዋንጫ ላይ ያተኩረ ግብ ሰንቀው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ፣ የደሞዙ የገንዘብ ምንጭ በጥረት ከተሰባሰበ ገቢ ሳይሆን ከመንግስት ካዘና መሆኑ፣ የስምምነት ፊርማዎች በአንድ አመት የመገደብ ባህል መለመዱ፣ የሚሉ ይገኙበታል። ለደሞዝ የሚውለው ገንዘብ ምንጩ የመንግስት ካዘና መሆኑ ለክፍያው መናር እንደምክንያት እንደሚጠቀስም የጥናቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር ዙሪያ በተጠቀሱት እክሎች የተነሳ የተለያዩ መስተጓጉሎች በሊጉ ውድድሮች ላይ መድረሱን እንዲሁም ለደሞዝ የሚወጣውን ገንዘብ የሚመጥን ጥልቅ ምዘና በተጫዋቾቹ ዙሪያ አለመተግበሩን የጥናቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። የብዙዎቹን ምልከታ በሚገልጽ መልኩ የተጫዋቾች ኤጀንት የሆኑ አንድ ተሳታፊ የሚከተለውን አጋርተዋል፦
"ክለቦች፣ እጅ ጠብቀው የሚኖሩ ሆነው፣ ለመክፈል ቃል የሚገቡት ግን ከአቅማቸው በላይ ነው። በገንዘብ አቅም ምክኒያት፣ ፎርፌ የተሰጠበት፣ የውድድር ዓመቱን ከ23 ዓመት በታች ባለው ቡድኑ የተጨረሰበት አጋጣሚ አለ። መክፈል አቅቷቸው ደግሞ፣ ክርክር፣ ሸንጎ፣ ፍርድ ቤት የሚሄዱ አሉ። ሲቀጥሩ እንኳን ተጫዋቾቹን ጥልቅ በሆነ የቴክኒክ አናልስስ /ትንተና/ እና የሃኪም የአካል ብቃት ፍተሻ ማድረግ አልተለመደም። ‘ልመነው እስኪ’ በሚል በባለፈው አመት ፐርፎርማንስ ነው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለተጫዋች ደሞዝ የሚያፈሰው" ብለዋል
የተጫዋቾች ደሞዝን በሚመለከት በተሳታፊዎቹ በስፋት የተነሱ ነጥቦችን አንድ ፌዴሬሽኑን ወክለው በጥናቱ ከተካፈሉ ተሳታፊ በሚከተለው እይታቸው ያንጸባርቁታል።
"በተጫዋቾች ክፍያ ዙሪያ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ተጫዋቾቹ የሚከፍሉትን ታክስ ለሊጉ ሊያቀርቡ ይገባል። ለተጫዋቾች የሚቀርበው የማበረታቻ ክፍያ … ሊጤን ይገባል። የማበረታቻው ልዩነት፣ 3 ሺህ የሚቀርብለት ተጫዋች 25 ሺህ ከሚቀርበለት ተጫዋች ጋር የመደራደር ክፍተትን የሚፈጥር መሆን የለበትም። ክለቦች በመሰረት ልማት ግንባታ እንዲሰማሩ እየተጠበቀ፣ በአሁኑ ወቅት ገቢያው የሚመራውን የደሞዝ ክፍያ እንዲቋቋሙ መጠበቅ አግባብ አይደለም። እነ ጨርቃጨርቅ፣ ምድር ባቡር፣ ሙገር ሲሚንቶ ያሉ ከለባት የመለማመጃ ቦታ እና የማረፊያ ቦታ ነበራቸው። ነገር ግን ቋሚ እሴቶች ላይ እየሰሩ በአንድ በኩል፣ እየናረ የመጣውን የተጫዋቾች ደሞዝ በሌላ በኩል ሊቋቋሙት አልቻሉም። ነገር ግን እነሱ የሰሩት ቋሚ ሃብት ለሌሎች ይተርፋል። ይህ የሚያሳይህ፣ ጤነኛ ያለሆነ የተጫዋቾች ክፍያ እንዳለ እና ለስፖርቱ እድገት ለሚተጋ፣ ያለው ሲስተም የማይመች መሆኑን ነው" ብለዋል
ምክረ- ሃሳብ፦ ለአገራችን እግር ኳስ ገጽታ እና ለሌሎች ራሳቸውን በአግባቡ ለሚያስተዳድሩ ጥቂት ክለቦች ስኬት፣ የተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ አስተዳደር መመሪያ ላይ ሁለት አማራጭ መንገድ በምክረ ሃሳብነት ቀርቧል (እዚህ ጋር፣ ዝርዝር የመፍትሄ ሃሳቡ በዋናው ጥናት የቀረበ እና በዚህ ጽሁፍ ለአንባቢያን ባጠረ መልኩ የመፍትሄ ሃሳቡ የቀረበ መሆኑን መግለጽ ይጋባል)፦ አማራጭ አንድ፦ የአንድ የውድድር ዘመን የበጀት አመትን የፋይናንስ ዝርዝር እቅድ ከደብዳቤ ጋር አያይዞ ማቅረብ። ይህም በአንድ ውድድር ዘመን ሊፈጠሩ ለሚችሉ ክፍተቶች ቀጥተኛ ተጠያቂነትን ያመጣል፤ አማራጭ ሁለት፦ አንድ ክለብ፣ የባንክ ሂሳብ መዝገቡን /bank book or bank statement/ ከዝርዝር የአመቱ የበጀት እቅድ ጋር አያይዞ ማቅረብ። የባንክ ሂሳብ መዝገብ ውስጥ ተቀምጦ የሚታየው የገንዘብ መጠን በአመቱ በጀት ውስጥ ከተጠቀሰው የወጪ መጠን መብለጥ ወይም እኩል መሆን አለበት። ሁለቱም የአማራጭ መንገዶችን በመተግበር ሂደት ውስጥ፣ ለአላማው መተግበር የሚቀርቡ ሰነዶች በሊጉ እና በክለቦች መካከል ብቻ በሚስጥር የሚቀመጡ መሆናቸውን ሊጉ የማስተማመኛ ደብዳቤ ሊያቀርብ ይገባል። ክለቦች ወደ ውድድር ለመግባትም ሊቀላቀሉ የሚቸሉት ከሚያሟሏቸው አመታዊ መስፈርቶች መካከል አንዱ ይህ ይሆናል።
ከዚህ በፊት አንደተጠቆመውም ተጫዋቾች የደሞዝ ታክስ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሊጠየቅ ይገባል። ይህ ሪፖርት እና ሌሎች ለአላማው መተግበር በማንኛወም አካል የሚቀርቡ ሰነዶች በሊጉ እና በአቅራቢው መካከል ብቻ በሚስጥር የሚቀመጡ መሆናቸውን ሊጉ የማስተማመኛ ሰነድ ሊያቀርብ ይገባል።
ይህ አሰራር ከሚያስገኘው የአሰራር ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባሻገር የክለቦችን እውነተኛ የመክፈል አቅምን ማመላከት ያስችላል፤ ተጫዋቾች የተስማሙበትን ደሞዝ (እና በወቅቱ) እንዲያገኙ ዋስትና ይሰጣል፤ በአንድ የውድድር ዘመን ውድድራቸውን የጀመሩ ክለቦች ውድድራቸውን እንደሚጨርሱ ለሊጉ ማስተማመኛ መስጫ አንድ መንገድ ሆኖ ያገለግላል። ለዚሁም የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር መመሪያ ማውጣት የግድ ይላል። ይህም ከሚያካትታቸው መካካል በበርካታ አገራት እንደሚከናወነው፣ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት ክለባት የውድድር ዘመናቸውን የሚያስጨርሳቸውን ገንዘብ በአካውንታቸው መኖሩን ማሳየት መቻል አለባቸው። በተያያዘም፣ ዲሲፕሊን እና ፐርፎርማንስ ጋር የተያያዘ የውል ማቋረጥ መስፈርቶች በግልጽ ሊቀረጹ ይገባል። በተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር መመሪያ ውስጥ ከሚካተቱ ቁልፍ ነጥቦች መካከል የፊርማ፣ የማበረታቻ፣ የመደጎሚያ ክፍያዎች ይገኙበታል። ይህ አሰራር በአውሮፓ እና አሜሪካ ያሉ ሊጎች ዘንድ የተለመደ አሰራር ሲሆን፣ በዋናነት ክፍያዎች ሊያስከትሉት የሚችሉትን የፋይናንስ ቀውስ አስቀድሞ ለመቋቋም ያስችላል።
የገቢ ምንጮችን ማስፋፋት
የገቢ ምንጮች ማስፋፋትን በሚመለከት በተደጋጋሚ ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል እግር ኳሱ ያለበት አንዱ ፈታኝ ነባራዊ ሁኔታ እንደሆነ ተመልክቷል። በተለይ፣ ክለቦች እግር ኳሱን እንደቢዝነስ የሚያዩበት አሰራር ያልተለመደ መሆኑን እና በጉዳዩ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በብዛት ተነስቷል።
የቡድን አርማ የያዙ ቁሳቁሶች ሽያጭ፣ የሚዲያ መብት ሽያጭ፣ ስፖንሰርሺፕ (የቡድን፣ የመለያ፣ የስም መጠሪያ)፣ የተጫዋቾች ግብይት፣ የተለያዩ የትኬት ሽያጮች፣ የስታዲየም ውስጥ አገልግሎቶች ሽያጭ፣ ወዘተ ያሉ የገቢ ምንጮችን ወደ ገንዘብ የመቀየር አሰራር በክለቦች ዘንድ መዳበር የሚገባው ነው።
በተለይ፣ ሌሎች አገሮች ከእነዚህ የገቢ ምንጮች የሚያሰባስቡት የገንዘብ መጠን ሲቃኝ፣ በአገራችን እየባከነ ያለ ሰፊ ሃብት መኖሩን ያመለክታል። በተለይ፣ ክለቦች የአካባቢያዊ መንግስት በጀት ጥገኛ መሆናቸው፣ በፈጠራ ላይ የታገዙ ዘዴዎችን ተጠቅመው ገቢ የማሰባሰብ ተነሳሽነታቸው ላይ የራሱን አሉታዊ ተጸዕኖ እንዳሳደረ ጠቁመዋል። ክለቦች ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ አማራጮችን በመፍጠር፣ የመንግስት በጀትን ደረጃ በደረጃ ወደ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያውሉበትን መንገድ የመቅረጽ ቀጣይ ሃላፊነት የሊጉ እንዲሆንም ተሳታፊዎች በአጽዕኖት ጠይቀዋል። በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ነገር ግን ተመሳሳይነት ያላቸው እይታዎች የተጋሩ ሲሆን፣ የብዙዎቹን አተያየት በሚወክል መንገድ፣ የክለብ አስተዳደር የሆኑ ተሳታፊ የሚከተለውን አካፍለዋል፦
“ክለቦች የራሳቸውን የገቢ ምንጭ አስፍተው መንቀሳቀሳቸው፣ መንግስትን ራሱን ቀጣዩን በጀት ለመልቀቅ የሚያበረታታ ይሆናል። ለምሳሌ፣ የሶስት ዓመት ስፖንሰር ብትፈራረም ለክለቡ ገቢ ነው፣ የክለቡ ባለቤት ለሆነው የከተማው መንግሰት ደግሞ የሶስት አመት ዕዳም፣ ሃላፊነትም ነው። እና፣ ገቢን ማሳደግ የተሳሰረ ጠቀሜታ አለው" ብለዋል።
ገቢ የማመንጨት ልምድን በሚመለከት የብዙ ተሳታፊዎችን ምልከታ፣ አንድ ደጋፊ የጥናቱ ተሳታፊ እንደሚከተለው አጋርተዋል፦
"እየባክኑ ያሉ ብዙ የገቢ ዕድሎች አሉ። ለምሳሌ፣ ‘ስንቱ ክለብ ነው በሚጫወትበት ሰዓት ስፖንሰሮቹን እያሰተዋወቀ ያለው?’ ስቴዲየሙም፣ የቲቪ ስክሪኑም እኮ ባዶ ነው። ገንዘቡ አነሰም በዛ፣ በስርጭት ወቅት የሚታይ ነገር የለም። ይህም ማለት መገኘት የሚችል ሃብት እየባከነ ነው።" ብለዋል
ገቢን በማሳደግ ዙሪያ፣ የተጫዋቾች ዝውውር እና የዝውውር ገቢያ ባህል ሊዳብር እንደሚገባው ተሳታፊዎች አንስተዋል። በገቢ ማሰባሰብ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎች ለረጅም ጊዜ የተንከባለሉ የጥልቅ እና ውስብስብ ችግሮች ውጤት መሆናቸውን ተሳታፊዎች አንስተው፣ በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሁለገብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
ምክረ ሃሳብ፦ ክለቦች የገቢ ማስፋፊያ ቢያንስ የሶስት አመት እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ሊጠየቅ ይገባል። አሰራሩን ለማዳበር፣ የአለፈውን አመት ዕቅድ ያሳኩ ክለባት የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት በተያዘው አመት ማጠናቀቂያ ላይ እንዲቀርብላቸው ይመከራል።
የገቢ ምንጮች አስተዳደርን በሚመለከት የስፖርት ቢዝነስ ማናጀመንት ስልጠና ለክለቦች አመራሮች ሊሠጣቸው ይገባል። ክለቦች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸው መስኮች በሶስት ይከፈላሉ፦ ቀጥተኛ፣ ተዛማጅ እና አጋዥ የገቢ ማግኛ መስኮች ወይም መንገዶች ናቸው።
ሀ) ክለቦች ቀጥተኛ የገቢ ምንጫቸውን ከስፖንሰርሺፕ፣ ከአካባቢያዊ የመገናኛ ብዙሃን የመብት ሽያጭ፣ የንግድ ምልክት ከያዙ ቁሳቁሶች የመብት ሽያጭ፣ ከስቴዲየም ትኬት፣ ከስታዲየም ውስጥ የእንግዳ መስተንግዶ ሽያጭ፣ ከተጫዋቾች ሽያጭና ከመሳሰሉት ማግኘት ይችላሉ።
ለ) ተዛማጅ የገቢ ምንጫቸውን ለማግኘት ደግሞ የሆቴል፣ የሬስቶራንት፣ የትጥቅ ማምረቻ ፣ የትራንስፖርት ንግድ፣ እና የኢነርጂ ምግብ እና መጠጥ አማራጮችን መጠቀም ይችላሉ ። የተዛማጅ ምንጮች፣ በአብዛኛው ወጪ የሚቀንሱ ሲሆኑ፣ በጊዜ ሂደት ወደ ገቢ ማመንጨት ሊደራጁ ይችላሉ። እኝህን የገቢ ምንጮች ተግባራዊ ለማድረግ፣ ክለቦች በሊዝ በመከራየት ሊያከናወኑ ይቻላሉ።
ሐ) አጋዥ የገቢ ማግኛ መስኮች ከሚያካትታቸው መካከል ደግሞ ካፌ፣ ባዛር፣ ኮንሰርት፣ ብዙሃኑን ያሳተፈ ሩጫ፣ የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ተዛማጅ እና አጋዥ የገቢ ማግኛ መስኮች በባለቤትነት፣ በግዥ እና በሊዝ ወይም በኮንትራት ኪራይ ሊከናወኑ ይችላሉ።
ክለቦች በተለያዩ የንግድ ስራዎች በነጻነት እንዲሰማሩ፣ ወደ ህዝብነት ተለውጠው የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል።
የኢትዮጵያ ክለቦች ችግሮች ዘርፈ ብዙ ነው። ጽሁፉ በተከታታይ ክፍሎች የተሰናዳ ሲሆን አራተኛውን እና የመጨረሻውን የጥናቱ ግምገማ በቅርቡ እናቀርባለን
ስለ ፀሀፊው፦
ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ እንዲሁም በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል የ5 ዶክትሬት ተማሪዎች አማካሪ ናቸው። ዶ/ር ጋሻው በስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። እስካሁን 10 መፅሀፍትን አሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢዎች አቅርበዋል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
የቦ ታክስ
ለዲያስፓራ አባላት በሙሉ እንዲሁም አሁን ኢትዮጵያ ላላችሁ። የአሜሪካ ታክሳችሁን ካላችሁበት ሆናችሁ እንድታሰሩ ነገሮችን ሁሉ አናስተካክላለናል። ያልተሰራ የታክስ ውዝፍ (Back Tax)፣ መስተካከል ያለበት ታክስ (Amendment) እንችላለን። የዚህ አመት ታክስ እና ሌሎችንም እንሰራለን።በViberም ሆነ Whatspp ይደውሉልን። ስልክ ቁጥራችን 619 255 5530 ነው ። YebboTax info@yebbo.com Yebbo.com
Translate
Do you need Ethiopian Power of Attorney where your agent can preform several crucial tasks on your behalf? Such as adoption proceedings, buying movable or immovable properties, paying tax, represent you in governmental and public offices and several others tasks with our your physical presence? If your answer is yes get the Ethiopian Power of Attorney or YEBBO now on sale
Shop Amazon
Call Yebbo
የቦ ኮሚኒኬሽን ኔት ወርክ ፣
ለ25 አመታት በላይ የስራ ልምድ ያካበተው
የእናንተው በእናንተው።
ከምሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ
የውክልና አገልግሎት መስጠት
የኢትዮጵያ ፓስፖርት አገልግሎት መስጠት
የቢጫ ካርድ የማውጣት አገልግሎት
የታክስ አገልግሎት መስጠት (የትም የኢትዮጵያ ግዛት ይኑሩ)
የጉዞ ወኪል
የትርጉም ስራ አገልግሎት
ለበለጠ መረጃ በስልክ ቁጥር
619-255-5530 ይደውሉ።
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.