Shop Amazon

Monday, January 3, 2022

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ሕልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳን ያስደነገጠና የኢትዮጵያውያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ሕልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳን ያስደነገጠና የኢትዮጵያውያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው - አቶ አወል አርባ
*******************
"ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ሕልውና ያደረገው ተጋድሎ ባንዳና ጠላትን ያስደነገጠና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ነው'' ሲሉ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ፡፡

ዳያስፖራው በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦችና ተቋማት በመደገፍ ረገድ እያደረገው ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአፋር ክልል ርእሰ መዲና ሰመራ የዳያስፖራ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አወል አርባና የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

ርእሰ መስተዳደሩ በዚህን ወቅት ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ህልውና ዘመቻ አኩሪ ታሪክ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

በ "#NoMore" ንቅናቄ ብርቱ ተጋድሎ አድርጋችኋል፤ ጫና ለማድረግ የሚፈልጉ አካላትን ደግሞ አሳፍራችኋል" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ንቅናቄው ለባንዳና ጠላት ትልቅ ድንጋጤ የፈጠረና የኢትዮጵያውያንን አንድነት በተግባር ያሳየ ሁነት መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ፤ በርካቶች በጅምላ እንዲጨፈጨፉ፣ ሴቶች እንዲደፈሩ ማድረጉንና በዚህም ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር እንዳሳየ ተናግረዋል።

የአፋር ህዝብ በአፋር በኩል ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል በተግባር ማረጋገጡን አንስተው፤ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ህልውና ዳግም የአድዋ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

አፋርን በተለይም "ሚሌን ይዤ መደራደሪያ አደርጋለሁ' ያለው አሸባሪ ቡድኑ፤ የጸጥታ መዋቅሩ ከአፋር ህዝብ ጋር የእግር እሳት ሆኖበት ተመልሷል ብለዋል።

ድሉ በአገር ውስጥና የውጭ ኢትዮጵያውያን ርብርብ እንደተገኘ ሁሉ አሁንም በአገር ግንባታው ሌላ ድል መቀዳጀት ይጠይቀናል ብለዋል።

"ኢትዮጵያን በአፋር በኩል መቼም መንካት እንደማይቻል አረጋግጣለሁ" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጃኬት የሚወልቅና የሚለበስ እንዳልሆነ ዳያስፖራው በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ዳያስፖራው ከዚህ ቀደም ሲያደርግ ለነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመስግነው፣ በቀጣይም በመልሶ ግንባታው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጠይቀዋል።

ለበርካታ ኢንቬስትመንት አማራጮች በታደለውና የቱሪስት መዳረሻዎች በተቸረው አፋር ክልል ኢንቬስት በማድረግ እንዲሳተፉና አገርና ወገን እንዲጠቅሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና እንደወርቅ ተፈትና እያለፈች ነው፤ በዚህም ትውልዱ ደማቅ ታሪክ እየፃፈ ይገኛል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግፍና ያደረሰው ውድመት የባዕድ አገር ወራሪ እንኳ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይገመት መሆኑን ጠቅሰው፤ "ያጋጠመንን ችግር ተጋግዘን ማለፍ አለብን" ነው ያሉት፡፡

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣቱ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከመምጣታቸው በፊትም በየአገራቱ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ታሪክ የማይረሳው ታላቅ ጀብድ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

"ወደ አገር ቤት መምጣታችሁ ዜጎቻቸውን እንዲወጡ የሚወተውቱ ጠላቶችን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ያጋለጠና ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በአፋር ክልል በአካል መገኘታችሁ ለክልሉ መልሶ ግንባታ አሻራ ለማስቀመጥ የምትጀምሩበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ ለአገረ መንግስት ግንባታ ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment