Shop Amazon

Tuesday, January 4, 2022

.ለጠላት የእሳት ነበልባል የሆኑት አባት እና ልጅ

ለጠላት የእሳት ነበልባል የሆኑት አባት እና ልጅ

አቶ ጋሻዉ ሹምዬ ይባላሉ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን በደባርቅ ወረዳ የድብ ባሕር ቀበሌ ነዋሪ እና የስምንት ልጆች አባት ናቸዉ። አብሮ ዘማች የበኩር ልጃቸው ደግሞ ደረጀ ጋሻው ይባላል፡፡ አባት እና ልጅ ሀገር ለማፍረስ ወደ አካባቢያቸው የመጣዉን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በምን መልኩ መደምሰስ እና መቀበሪያውን እዚያዉ ማድረግ እንደሚችሉ ተማከሩ፤ አደረጉትም። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ነሐሴ እና ጳጉሜን ወራት በአካባቢያቸው የፈጸመውን ወረራ ለመመከት ከወገን ጦር ጋር አብረው ተፋልመዋል፡፡ 

አባት እና ልጅ በወገን ጦር በደረሰበት ከባድ ምት የተፍረከረከውን አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድን እየተከታተሉ በመልቀም እና ዋሻ ውስጥ ተቆርጠዉ የቀሩትን የቡድኑን አባላት በመፋለም ሦስቱን አቁስለዉ አምስቱን ማርከዉ በአጠቃላይ ስምንቱን ለመከላከያ ሠራዊት አስረክበዋል፡፡ 

ጀግናው አቶ ጋሻዉ “አባቴ አርበኛ ነዉ፤ የአባቴን መሳሪያ ይዤ ነዉ የዘመትኩት፤ የእርሱ ልጅ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፤ ይህም ጠንክሬ ሀገሬን ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እንድታደግ አድርጎኛል” ነው ያሉን፡፡ ጀግናው አቶ ጋሻው አሁንም ስሜታቸዉ እንደጋለ፤ ደማቸዉ እንደሞቀ ነዉ፤ ሀገራቸውን ለማፍረስ የመጣውን ጠላት ደምስሰውታል። 

የበኩር ልጃቸዉ ደረጀ ጋሻዉ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ነበር የተመረቀዉ፤ ገና ሥራ ይዞ አዲስ ሕይወት ሳይጀምር ነበር ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የመጣን አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ ሀገራዊ ጥሪዉን ተቀብሎ ከአባቱ ጋር የዘመተዉ። 

“ሀገራችን ወረራ ሲፈፀምባት ቆሞ የሚያይ በዝምታ የሚያልፍ ወጣት የለም፤ እኔም እስከመጨረሻዉ ጠላቷን ልደመስስላት ነዉ ወደ ትግሉ የተቀላቀልኩት” ያለዉ ወጣት ደረጀ እጁ ላይ የተወሰነ ጉዳት ደርሶበት ሕክምና አድርጎ ወደ ግንባር መዝመቱን ተናግሯል።

“ታላቅ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ የሚከፈልላት ዋጋ ከመቁሰልም በላይ ነዉ” ሲል ነው ወጣቱ የገለጸው፡፡ 

“የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን እጅጉን ልንኮራ ይገባል፤ ሁላችንም የእነርሱን የጀግንነት ታሪክ በመድገም አሻራችንን እናሳርፍ” ብሏል። 

ዛሬም አዳዲስ ጀግኖች ተፈጥረዋል፤ እኛም የሠሩትን ገድል መግለጣችንን እንቀጥላለን።
Source Amhara Communications

No comments:

Post a Comment