የሲዳማ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀዋሳ ላይ ምክክር ማካሄድ ጀምረዋል
**********************
የሲዳማ ክልል የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀዋሳ ላይ ምክክር ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን በዚህ የምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፍ አቶ አብርሃም ማርሻሎን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ በከሃዲው የሽብር ቡድን የተቃጣብንንና ያለፍላጎት ተገደን ያካሄድነውን ጦርነት ክብሩንና ልዕልናውን ላለማስደፈር በቆረጠው ከመላው የሀገራችን ህዝብና ከጀግናው መከላከያ ኃይላችን ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋግጠናል፣ድል ተቀዳጅተናል፣የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን ቅስም ሰብረናል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም አሁን ላይ አንድ በመሆናችን ያገኘነውን ድል በልማቱም አንድ ሆነን የተጎዱ ወገኖቻችንን በመደገፍና የኢኮኖሚያችንን ጉዳት እንዲያገግም የማድረጉ ስራ ትኩረታችንን ከማድረግ ጎን ለጎን የሀገራችንንና የክልላችንን ሰላም ተደራጅተን መጠበቅ ይኖርብናልም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ነክቶ በቀላሉ መመለስ እንደማይቻልና ኢትዮጵያዊነት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ መሆኑን በሁሉም ኢትዮጵያውያን በውጭና በሀገር ውስጥ ህዝባዊ ማእበልና ወኔ ማየት ችለናል፤ ይህም ለኛ ትልቅ ድል ለጠላት ደግሞ ትልቅ ፍርሃትንና ሽንፈትን አከናንቧል ብለዋል።
"ለድላችን መገኘት በተናጠል የተደረገ ትግል የለም፤በተናጠል የመጣ ድልም የለም" በማለት የክልሉ ር/መስተዳድሩ ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ አክለውም በመድረኩ አንስተው፤ ድሉም የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው በማለት ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው በጠላት የተነካውና የተደፈረው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ ምክንያት ከዳር እስከ ዳር ተደራጅቶ፣ ተደጋግፎና ተጠናክሮ የፊትና የኃላ ደጀን በመሆን በግንባር በአካል ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን አብሮ እስከመቆም ታሪክ የማይረሳውን ደጀንነቱን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አረጋግጧል ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም እንደገለፁት ድሉን ከነባራዊ እውኔታና ሃቅ ውጭ መጠምዘዝም ማድረግም የማይቻልና ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ህዝብ ብቻ መሆኑንና አሸናፊዋም ኢትዮጵያ መሆኑን ጨምረው አንስተዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮቻችን ከድህረ ጦርነት በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በመጨረሻም በዚህ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ አመራሩ በጉዳዩ ላይ ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በድህረ ጦርነትና ከዚያ በኃላ ባለው ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ የፀጥታና የሰብአዊ ጉዳዮች ሁኔታዎች ላይ በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፍ ውይይትና ምክክር ካደረገ በኃላ ይህንን ተግባር ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማመጋገብ በብቃት ለመምራት የማስቻል በሚቀመጡ የጋራ አቅጣጫዎች ላይ በመግባባት ምክክሩ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment