የክልሉን አቅም እና የዜጎችን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ሊተለም ይገባል፦ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)
**************************
የክልሉን አቅም እና የዜጎችን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ሊተለም እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የገቢ ንቅናቄ ፍኖተ ካርታ አውደ ጥናት በባህርዳር እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ክልሉ ባለው አቅም፣ እንቅስቃሴ እና በሚጠበቅበት መጠን ግብር ለመሰብሰብ ተግዳሮቶች እንዳሉ አንስተዋል።
በመሆኑም ገቢዎች ቢሮ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት የግብር አሰባሰብ ፍኖተ ካርታው ይታዩ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ ገቢ ከሕዝቡ ቁጥር፣ ከመልማት አቅም እና በጦርነቱ ከገጠመው ውድመት አኳያ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪዎች ቡድንም የገቢ አሰባሰብ ችግሮች፣ መፍትሔዎች እና ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ጥናት አቅርበዋል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ምሁራን፣ የግብር አምባሳደሮች እና በዘርፉ የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በራሔል ፍሬው
No comments:
Post a Comment