Shop Amazon
Tuesday, April 2, 2024
በአዲስ አበባ የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን ላይ በድጋሚ ማሻሻያ ተደረገ
በአዲስ አበባ የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን ላይ በድጋሚ ማሻሻያ ተደረገ
◉ በአዲሱ መመሪያ መመሪያ 34 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው የቤት ሽያጭ ዋጋ ማሻሻያ ላይ ከሕብረተሰቡ በርካታ ቅሬታዎች በመቅረባቸው፣ መመሪያው በድጋሚ እንዲከለስ ተደርጓል።
ትናንት መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በተሠራጨው አዲስ መመሪያ በኮንዶሚኒየም ቤቶች እና በአፓርታማዎች ሽያጭ የካሬ ሜትር ዋጋ ላይ በአማካኝ 34 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል። በአፓርታማና በኮንዶሚኒየም ቤቶች ሽያጭ ስሌት ላይም እንዲሁ ጉልህ ቅናሽ ተደርጓል።
የከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በጋራ ባካሄዱት ጥናት የተዘጋጀው ማኑዋል በቤት ሽያጭ ገቢ ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲያመጣ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ደሲሳ ፊርማ ለሁሉም ክፍለ ከተሞች በተሰራጨው መመሪያ እንደተመለከተው፣ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ለአብነት ደረጃ አንድ በተባሉ አካባቢዎች የሚሸጥ የአንድ አፓርታማ ቤት ዋጋ በካሬ ሜትር 132,200 ብር፣ በተመሳሳይ በዚሁ ደረጃ አንድ አካባቢ የኮንዶሚንየም ቤቶች ሽያጭ ዋጋ ደግሞ በካሬ ሜትር 72,300 ብር በሚል ቁርጥ ዋጋ ወጥቶላቸው የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ማኑዋል ይህ ቁርጥ ዋጋ በ34 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል።
የከተማው አስተዳደር የቤት ሽያጭ ግብይት ላይ አዲስ ማንዋል ለማውጣት የተገደደው፣ በግብይት ወቅት መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እና የሚቀርበው የሽያጭ ውል እጅግ የተራራቀ በመሆኑ ነው ተብሏል።
በውሉ ላይ ተመስርቶ ከሚገኘው ካፒታል ዕድገት ታክስ 15%፣ ቫት 15%፣ የቴምብር ቀረጥ 2%፣ አሹራ 4% ፣ እንደየገቢው ሁኔታ ከ10 - 35 % ትርፍ ግብር በተሰኙ የገቢ አርዕስቶች ላይ የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች እየተደረደሩ በሽያጭ የሚገኝ ገቢ እንዲደበቅ ተደርጓል የሚል ነው።
በቤት ግብይት ዙሪያ አሳንሶ መዋዋል፣ አሳንሶ መገመት፣ የስም ዝውውር ማዘግየት፣ ቤቱ ለበርካታ ጊዜያት ግብይት ቢፈፀምበትም በመንደር ውል የስም ዝውውር አገልግሎት ሳይጠይቁ ግብይቱን አለማሳወቅ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸው ተመልክቷል።
ይህ የተበላሸ አሠራር የከተማውን የመሬት ስሪት ባለሙያዎች ሲያሳስብ የቆየ ችግር ቢሆንም ዘግይቶም ቢሆን የከንቲባ አዳነች አቤቤ ካቢኔ ችግሩን ለመፍታት ውሳኔ አሳልፏል።
የከተማው አስተዳደር አሰራሩን በማስተካከል - ዕውነተኛው የሽያጭ ፍሬ ገንዘብ ላይ ያደርሰኛል በማለት እንደየ ቦታው ደረጃ - አንድ ይዞታ በካሬ ሜትር ሊሸጥ የሚችልበትን ዋጋ ወስኗል።
በአዲሱ ቀመር ቤት ሻጭ እና ገዥ የሚያቀርቡት ውል ላይ የጠቀሱት ገንዘብ ከተቀመጠው የካሬ ሜትር ዋጋ ከበለጠ ተቀባይነት የሚያገኝ ሲሆን ካነሰ ደግሞ አስተዳደሩ ባቀረበው የካሬ ሜትር ዋጋ ብቻ ይስተናገዳል።
የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን በቦታው ስፋት በማባዛት የሚገኘው ውጤት ከሽያጭ ውሉ ጋር በማነፃፀር ብልጫ ባለው ዋጋ ስመ - ንብረት ዝውውሩ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተመልክቷል።
ምንጭ:- WZ news / ውድነህ ዘነበ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment