Shop Amazon

Showing posts with label dire dawa. Show all posts
Showing posts with label dire dawa. Show all posts

Tuesday, February 4, 2020

የጅብ መንጋ በድሬዳዋ ከተማ ስጋት አሳድሯል ተባለ

የጅብ መንጋ በድሬዳዋ ከተማ ስጋት አሳድሯል ተባለ
*********************************

በድሬዳዋ ከተማ የገንደ ሮቃ አካባቢ ነዋሪዎች የጅብ መንጋ ጥቃት እያደረሰባቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲፈልግላቸው ጠየቁ።

ባለፈው ቅዳሜ አንድ የ3 ዓመት ህፃን በመንጋው ህይወቱ አልፏል።

በድሬዳዋ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ልዩ ስሙ ገንደ ሮቃ ከሚባለው ገደላማ ስፍራ የወጣ የጅብ መንጋ በሰፈሩ በመጫወት ላይ ከነበሩ ህፃናት መካከል አንድ የ3 ዓመት ጨቅላ ህፃን አንጠልጥሎ ወስዷል።

ህፃናቱ ተደናግጠው ባሰሙት ጩኽት የሰፈሩ ሰው ግልብጥ ብሎ የወጣ ቢሆኑም በተለይ የተጠቂው ህፃን አባት እስከ የጅብ መንጋው ጎሮ ድረስ እየሮጠ በመከተል የአንዱን ጅብ ጭራ በመያዝ ጭምር የልጁን ህይወት ለማትረፍ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት መቅረቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢዜአ ተናግረዋል።

ህፃኑ በነዋሪው ርብርብ ከጅብ መንጋው ማስጣል ቢቻልም ጭንቅላቱ ላይ በጅብ ንክሻ የከፋ ጉዳት ስለደረሰበት ህይወቱ ማለፉን ወይዘሮ አልማዝ ዝናቡ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ገልፀዋል።

ከቀድሞ ምድር ባቡር ድርጅት፣ ከጉምሩክና ከምስራቅ አየር ኃይል በተለምዶ ሰባተኛ ከሚባለው የጦር ካምፕ የሚዋሰነው ገንደ ሮቃ የሚባለው መንደር ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥሻ እየተዋጠ በመምጣቱ የጅብ መንጋ የሚርመሰመስበት ስፍራ መሆኑን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

አቶ ታገል በንቲ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለፁት የጅብ መንጋው ከጎሮው እየወጣ ነዋሪዎችን ሲተናኮል በአንድ ወር ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

የጅብ መንጋው በአካባቢው እንዲርመሰመስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ከምድር ባቡር ድርጅት የፍሳሽ ቱቦዎች ፤ ከሰባተኛ ጦር ካምፕና ከጉምሩክ  የሚጣሉ ተረፈ ምርቶች የሚለቃቅመው ምግብ ፍለጋ ነው ተብሏል።

የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኮትሮባንድ የሚይዛቸው ከብቶችም  ለጅቦቹ መበራከት ምክንያት መሆኑን የአካባቢው ወጣት ካሳሁን ከበደ ተናግሯል፡፡
ወይዘሮ አለምነሽ ገዛኸኝ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ትናንት ጭምር አራት ጅቦች በአካባቢው ሲያንዣብቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ዳግም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይከሰት መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግለትም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

ገንደ ሮቃ የተባለው አካባቢ የሚገኝበት የቀበሌ 03 ቀበሌ መስተዳድር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ግርማ ስለሁኔታው ተጠይቀው በስፍራው የጅብ መንጋ መኖሩን በመግለፅ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ መፍትሄ ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

የጅብ መንጋው በመርዝ ከመግደል ይልቅ ጢሻውን በመመንጠር አካባቢውን ለቆ እንዲሔድ የማድረግ ስራ መጀመሩን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ባለሙያ አቶ ማሙሽ ዘውዱ በበኩላቸው የጅብ መንጋው ዘላቂ መፍትሔ እስኪፈለግለት ድረስ በስፍራው በሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች የተጠናከረ አጥር እንዲገነቡ መክረዋል።

የቀድሞ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስአኪያጅ አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ በበኩላቸው ጅቦች በድርጅቱ የጥገና አካባቢ በብዛት መኖራቸውን በመግለፅ  ችግር እንዳይፈጥሩ ከከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር ተባብረን እየሰራን እንገኛለን ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።