ሩብ ክፍለ ዘመን እንደዋዛ
————————————
(በጀሚል ይርጋ)
ታህሣስ 26/ 1985 ዓም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራን መገንጠል እውን የሚያደርገውን "ሪፈረንደም" የሚታዘቡ ልዑካንን መላኩ ‘ ጣልቃ ገብነትና የሪፈረንደሙም ሂደት የኢትዮዽያ ህዝብን ከወሳኝነት ያገለለ’ መሆኑን ፣ አዲስ አበባ ለጉብኝት ይገኙ ለነበሩት የወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ያካሄዱት በአጭር የተቀጨ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ሩብ ክፍለ ዘመን ሆነው – 25 ዓመታት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አዲስ አበባ እንደሚገቡ በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረበት ታህሳስ 24/ 1985 ምሽትና በቀጣዩ ቀን ባካሄዱት ስብሰባ ነበር ሰላማዊና ሁከት ያልተመላበት ተቃውሞ ለዋና ፀሀፊው ለማሰማት የወሰኑት።
ይሁን እንጂ፣ በውሳኔያቸው መሰረት ሰኞ ታህሳስ 26/1985 ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጡም ዋና ፀሀፊው ዘንድ ሳይደርሱ ገና ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንደወጡ ነበር የፀጥታ ሀይሎች (ታጣቂዎች) በወሰዱት የኃይል እርምጃ ሰልፉ የተበተነው። በወቅቱ የሰልፉን ሂደትና የመንግስትን እርምጃ እንደ ዘገቡት የነፃ ፕሬሶችና ኢሰመጉ ሪፖርት፣ ዓይነ ስውራንና ሴቶች ተማሪዎችን ጨምሮ ብዙዎች ተገድለዋል። ቆስለዋልም። የፀጥታ ኃይሎቹ ሰልፉን ለመበተን የተጠቀሙባቸው መሳሪያዎች ጥይት፣ ዱላና ጩቤ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።
መንግስትና መንግስታዊ ሚዲያዎች በበኩላቸው፣ ሰላማዊ ሰልፉ ህገ ወጥና ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን፣ እንዲሁም ሰልፉን ለመበተን በተወሰደው እርምጃም ተስፋሁን ወርቁ የተባለ አንድ ተማሪ መገደሉንና ጥቂቶችም መቁሰላቸውን አሳውቋል። ይሁን እንጂ ይህን የመንግስት መግለጫና ጉዳቱን የገለፀበት አኃዛዊ መረጃ፣ ኢሰመጉና ሌሎች የውጭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችና የነፃው ፕሬስ፣ እውነታውን ያደበሰበሰ ነው ሲሉ ክፉኛ ነበር የተቹት።
በተቃውሞውና ተቃውሞውን ተከትሎ በደረሰው ጥፋት ዙሪያም በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ካውንስል ፕሬዝዳንት የነበረው ጋሻው ካሤ እና ሌሎች የካውንስሉ አመራሮች፣ ከምሁራን ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ፣ ዶ/ር መኮንን ቢሻው፣ ዶ/ር እሸቱ ጮሌና ሌሎችም በተለያዩ የግሉ ፕሬስ የህትመት ውጤቶች በቃለ–ምልልስ መልክ ሰፊ አስተያየቶችን ሰጥተውበት ነበር። ቆስለው ሆስፒታል የተኙና በተቃውሞው ተሳታፊ የነበሩትም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። እናም የወቅቱ ኹነት ምን ይመስል እንደነበር በሰፊው ለመረዳት ያስችላችሁ ዘንድ እነዚህን መፅሄቶች ፈላልጋችሁ ታነቧቸው ዘንድ እጋብዛችኋለሁ። እግረ መንገዳችሁንም የዚያን ጊዜ ተማሪዎች የተቃውሞ መንፈስና የዘንድሮውን አነፃፅራችሁ ትገመግሙበታላችሁ።
በበኩሌ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የያኔዎቹ ተማሪዎች ከሁሉም ብሔሮችና ሃይማኖቶች የተውጣጡ ቢሆኑም እንደ አሁኖቹ በገዛ ወንድሞቻቸው ላይ የሚዘምቱና እርስ በርሳቸው ተሻምቀው የሚገዳደሉ አልነበሩም። ስለ ሀገር ተቆርቁረው፣ ለሀገር የሚሞቱ እንጂ። ክብር ለነርሱ ይሁን !!!
(ለተቃውሞው 25ኛ ዓመት መታሰቢያ የተፃፈ)
– ታህሣስ 26/ 2010 ዓም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment