Shop Amazon

Friday, December 31, 2021

More than $ 250,000 seized in Addis Ababa

በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ250 ሺህ ዶላር በላይ  ተያዘ
****************************

የአሸባሪውን የህወሓትና የሸኔ ቡድንን እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ240 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና በአካውንታቸው ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲታገድ መደረጉን የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ ፡፡

በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ250 ሺህ ዶላር በላይ  መያዙን እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩትን ጨምሮ በተለያዩ  ወንጀሎች  የተሰማሩ በርካታ  ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንመ ግብረ ሀይሉ አመልክቷል፡፡ 

የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከመደበኛ የፀጥታ ስራው በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገር ውስጥ እያገቡ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ምቹትና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ዝግጅትና ስምሪት አድርጎ የጋራ ግብረ ኃይሉ እየተቀበለ ይገኛል፡፡ 

ይሁንና ከትልቁ ሀገራዊ ዓላማ በተቃራኒ የግል ጥቅማቸውን ለማግበስበስ የሚንቀሳቀሱ አንዳአንድ ህግወጦች በመገኘታቸው ህገወጥ ድርጊታቸውን ለማቆም በአዲስ አበባ በተለምዶ ኢትዮጵያ ሄቴል፣መርካቶና መሰል የጥቁር ገበያ ማዕከሎችና ሌሎች የሚጠረጠሩ አካባቢዎች በተካሄዱ ኦፕሬሸኖች በርካታ ተጠርጣሪዎች  በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል መግለጫው፡፡

የከተማዋን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በሚንቀሳቀሱ በእነዚህ ህግወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃም ከ250 ሺህ ዶላር በላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
 
መግለጫው አክሎም ከህገወጥ የግንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ ከ50 ሺህ በላይ ፓውንድ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች እና ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ የኢትዮጰያ ገንዘብ ከተጠርጣሪዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ህገወጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በተለምዶ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚኖር በአንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ ቤት ውስጥ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዘን ኦፓል እንዲሁም በከተማዋ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሀገራት የውጭ ገንዘቦች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ትናንሽ ታብሌቶች፣  ላፕቶፖች፣ የብር ጌጣጌጦች፣ የባንክ ሂሳብ ደብተሮች እና ፍላት ቴሌቪዥኖች መያዛቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ 

በተመሳሳይም ከአደንዘዥ እፅ ጋር በተያያዘ 5 አዘዋዋሪዎች መያዛቸውን ያመለከተው የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፤ የተለያዩ የተጭበረበረ ሰነዶችን በማዘጋጀት የተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎች እንዲሰሩ የሚያግዙ 7 ህገ-ወጥ ደላሎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያለውን የአሸባሪውን የህወሓትና የሸኔ ቡድንን እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ240 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና በአካውንታቸው ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲታገድ መደረጉንና ጉዳያቸውም በምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡  

ለእንግዶች ከእንግዳ ተቀባዩ ህዝባችን ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ነገር የተመቻቸ የማድረጉ ስራ እየተሰለጠ መሆኑን ያስታወቀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም የፀጥታ እና የደህንነት ችግር የትም ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚፈልጉትን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱን አመልክቷል፡፡

ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታና ለመረጃ አካላት የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡


No comments:

Post a Comment