Friday, November 2, 2018

ዶር አብይ በጀርመን ያደረጉት ንግግር (ሙሉ ንግግር)

ዶር አብይ በጀርመን ያደረጉት ንግግር (ሙሉ ንግግር)
...............................................

አይነን ሾነን ጉተን ታግ!

ኤይቶፒሼ ዲያስፖራስ ኢን ዶችላንድ ኡንት ኤይሮፓ!

ክቡራትና ክቡራን!

ከመላው አውሮፓ የተሰበሳባችሁ የሀገሬ ልጆች ሆይ፣ የማይንን ወንዝ ተገን አድርጋ በተቆረቆረችው፣ የገንዘብና የኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው ፍራንክፈርት ተናኝተን በአይነ ሥጋ መተያየታችንንን እንደ ታላቅ እድል እቆጥረዋለሁ።

ከሀገር የወጣችሁበት ዘመንና ምክንያት እንደ ቁጥራችሁ ብዙ፣ እንደየመጣችሁበት ሀገር ለየቅል መሆኑ ግልፅ ነው። ለትምህርትም ይሁን ለሥራ፣ በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ የተሰደዳችሁ ወገኖቼ… ከምንወዳት ሀገራችን እና ሁሌም ከምትናፍቁት ህዝባችን እጅግ የከበረ ሰላምታ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደዛሬው ከኋለኛው ተርታ ተመድባ በችግሯ ከመታወቋ በፊት ከአውሮፓ አገራት ጋር ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት ነበራት። ከእንግሊዝ ጋር በትምህርት፣ ከፈረንሳይ ጋር በባቡር ሀዲድ፣ ከፖርቱጋል- በጦር ትብብር፣ ከቱርክና ከግሪክ በንግድ፣ ከስዊድን በጤናና በአየር ሀይል፣ ከሩሲያና ከሌሎች የምስራቅ አውሮጳ ሀገራት ጋር በተለያዩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የነበረን ታሪካዊ ተዛምዶ እስከዛሬም የቀጠለ የወዳጅነታችን መሠረት ነው። ከጀርመንም ጋር ቢሆን ጠንካራ ትስስር ነበረን።

አምስተኛዋ ግዙፍ የጀርመን ከተማ ፍራንክፈርት፣ የታዋቂው ደራሲ ዮሐን ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎይተ ከተማ ናት። በዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ስም የተቋቋመ ስመ ጥር ኢንስቲቲዩት በአገራችን ከመኖሩ በተጨማሪ የጀርመን የባህል ማዕከልና ትምህርት ቤት መቋቋሙ ጠንካራ ትስስርና ወዳጅነት ስለመኖሩ አንዱ ማሳያ ነው። እንደ አገር ከጀርመን ጋር፣ እንደ አጠቃላይ ደግሞ ከአውሮፓ ጋር ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ተመሳስሎም አለን።

እንደምታውቁት፣ ለእኛ የቅርብ ጊዜ እውነታ በሆነው ጦርነትና ግጭት ውስጥ ያላለፈ የአውሮፓ ሀገር የለም። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእጅጉ ከተጎዱት የአውሮፓ ከተሞች መካከል አንዷ ፍራንክፈርት ናት። ብዙ ሕዝብ አልቆባታል፤ መኖሪያ ቤቶቿ የሙታን መንደሮች መስለው ነበር፤ አያሌ የንግድና የገበያ ሥፍራዎቿ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ታዋቂ የነበረውና በወቅቱ ከጀርመን በታላቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ዋናው የንግድ መናኸሪያዋ ወድሟል። ሆኖም ግን፣ የማይበገሩትና ለችግር የማይረቱት ፍራንክፈርቶች ከተማቸውን እንደገና ገንብተው የአውሮፓ የፋይናንስ ማዕከል ለማድረግ ዐርባ ዓመት እንኳ አልፈጀባቸውም። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።

ሃያ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዓለማችን ታላላቅ ጦርነቶች የማስተናገድ ክፉ ዕጣ በላያቸው ላይ የተጫነባቸው አውሮፓውያን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቻቸውን አጥተዋል፤ ለዘመናት የተገነባ ታሪካቸው አመድ ሆኗል፤ የልዩነት ግንብ በመካከላቸው ተገንብቶ ቆይቷል። በዘመኑ፣ አውሮፓውያን እንኳንስ ለሌሎች ሕዝቦች መጠጊያ ሊሆኑ ይቅርና በገዛ ሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው ስደትን የመረጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም። ያ ሁሉ አበሳ የመጣው በጥቂቶች፣ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ በግል ጥቅማቸው በታወሩ መሪዎች እና የእኛ ዘር ከሁሉም ይበልጣል ባይ ደመ-ነፍሳውያን ቅዠት መሆኑ በጸጸት የሚታወስ ክፉ የጦርነቱ ጠባሳ ነው። የዚህ አሰቃቂ ጥፋት የፍጻሜ ትርፉ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ ስደት፣ ወረርሽኝና እልቂት ብቻ ነበረ።
ሆኖም ግን፣ ጠንካሮቹ አውሮፓውያን ከአንደኛውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እጅግ በፈጠነ ጊዜ አገግመው፣ ዛሬ ላይ እናንተን ጨምሮ ከመላው አለም ሚሊዮኖችን እስከማስጠለል ደርሰዋል። እርስበርስ መሸናነፍን ትተው አለምን ማሸነፍ ችለዋል። ይሄን ያሳኩት በአጋጣሚ አይደለም። ወገባቸውን አሥረው፣ ተስፋ መቁረጥን አባርረው፣ የደረሰባቸውን መከራ ሁሉ ለነገ ሲሉ ታግሠው፣ ለአገራቸው አንድ ሆነው በትጋት ስለሠሩ ብቻ ነው።

እዚህ ቦታ በፊታችሁ ስቆም ሀገራችን በኢኮኖሚ በልጽጋ፣ ሰላማችን ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ፤ ግጭት ጠፍቶ፣ ዴሞክራሲ ጎልብቶ፣ ሰብአዊ መብት በላቀ ሁኔታ ተከብሮ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር። ግን አይደለም። አሁን በእጃችን ያሉን ሁለት ነገሮች ናቸው። ነጻነትና ተስፋ። እነዚህን ሁለቱን ይዘን በትብብርና በአንድነት ከሰራን የምንሻት ኢትዮጵያን ከመፍጠር የሚያግደን የለም።

ከጦርነቱ ማግስት አውሮፓውያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከመገፈታተር ይልቅ ትብብርን የመረጡት ጥቅሙ ስለገባቸው ነው። ሕዝቡ ጦርነትን አምርሮ ቢጠላ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ስላየው ነው። ዘረኝነትንና የበላይነት አባዜን አምርሮ የተዋጋው ካደረሰበት ውድመትና ጥፋት ስለተረዳው ነው።

ይህ፣ እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠን ትምህርት ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ብዙዎቹ የለውጥ ጅምሮች በመሳሪያና በአመጽ ተጀምረው፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በማሳደድና በመሰደድ የተደመደሙ መሆናቸው ለሁላችን ግልፅ ነው። አዲስ የሰላምና የእርቅ ምዕራፍ ከመሆን ይልቅ የሌላ ዙር ውጊያ እና አመጽ መጀመሪያ የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር የትናንት ታሪካችን ምስክር ነው። አሁን፣ ያላየነውን የምናይበት፣ ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ዘመን ነው።  ምቾታችንን ተወት አድርገን፣ መከራዎቻችንን ታግሰን፣ ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራበት፤ ለአገራችን በተባበረ ክንድ የምንተጋበት ወቅት ነው። በየጎራው ያሉ ሀይሎች አሸናፊ የሚሆኑበትን የፖለቲካ ባህል ከአውሮፓ ተምረን እንደ አገር አሸናፊ የምንሆንበትን መንገድ መያዝ አለብን፤ ይገባናልም።
የተከበራችሁ ወገኖቼ!

ከሩቁ ሆናችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትሰሙ በአንድ በኩል ትደሰታላችሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትከፋላችሁ። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ታደርጋላችሁ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋ ትቆርጣላችሁ። ግን ርግጠኛ መሆን ያለባችሁ አንድ ነገር፣ ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክና መልክ እንደቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ርስት ሳትሆን፣ ዘመናትን ያስቆጠረች፣ ታላቅ ሕዝብ የመሠረታት፣ ታላቅ ሀገር መሆናን ነው። ‹እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው› እንደተባለው፣ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም፤ ደክማ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም፤ ቀጥና ይሆናል እንጂ አልተበጠሰችም። ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሳንከፋፈልና ጊዜያችንን የማይጠቅም ነገር ላይ ሳናባክን ወገባችን አጥብቀን ከሠራን አገራችንን ታላቅ ማድረግ የሚከብድ አይሆንም።
መቼም፣ ኢትጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያን ክፉ ማየት የሚመኝ ጤነኛ ሰው አለ ብዬ አላምንም። እዚህ ከተሰበሰባችሁ ያገሬ ልጆች መሀል የሀገሩ ነገር ሆዱን የማይበላው ውስጡን የማያንሰፈስፈው ሰው አይኖርም። ኢትዮጵያዊነትን ከቃላት በዘለለ እና ከስሜት በተሻገረ መልኩ በስራ የምናሳይበት ዘመን ላይ ስለሆንን ለጊዜው የማይጠቅመውን ትተን፣ የሚያስፈልገንን አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።

ወደድንም ጠላንም እንደ ሀገር ልንሸሻቸው በማንችላቸው ሦስት መሰረታዊ የጊዜ ማዕዘኖች መካከል ላይ እንገኛለን። ከትናንት ስህተቶቻችን የምናስተካክለው፣ ዛሬ ተግተን ልንሠራው የሚገባን፣ ለነገ ደግሞ የምንገነባው ሁነኛ መሠረት አለ። እነዚህን ሦስቱን አጣጥመን ለመሄድ በምናደርገው ትግል አንዳንድ ጊዜ ወደ አንዱ መጎተታችን አይቀሬ ነው። ከትናንት አያሌ መልካም ነገሮችን እንደወረስን ሁሉ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮችንም ወርሰናል። ፍትሕን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን፣ የዳበረ የሥራ ባሕልን፣ በሕግና በሥርዓት መኖርን፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጥን፣ ረሐብና ድህነትን ማስወገድን በተመለከተ ገና ብዙ የሚቀሩን ሥራዎች አሉ።

እነዚህን የምናሳካው በማንመልሰውና በማንቀይረው ትናንት ላይ እየተጨቃጨቅን፣ ወርቅ እድላችንንና ጊዜያችንን በማባከን ወይም ጥቂቶች በሚያዘጋጁልን አጀንዳዎች በመተራመስ ሳይሆን ልቦናችን የሚያውቀውን በጎ ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየር ነው። ጊዜውን መጣያ እንዳጣ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደን ውድ እውቀታችንና ጉልበታችንን በማፍሰስ ሳይሆን ትርጉም ያለው ስራ ላይ በመሰማራት ጭምር ነው። ጨለማውን ለመግፈፍ ሻማ ማብራት እንጂ የጨለማውን ክብደትና ጽልመት መስበክ መፍትሄ አይሆንም። እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁ በማለት እንጂ እነ እገሌ አገሬን ጉድ ሰሯት እያልን መዓት ብናወራ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ለሀገራችን ያለን ጥልቅ ፍቅር በግብር የሚገለጸው እምኑ ላይ ነው?

ክቡራንና ክቡራት

ፍትሕና ዴሞክራሲ ስለተፈለጉ ብቻ አይገኙም። በሰላማዊ ሰልፍና በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጠዋት ተዘርተው ማታ የሚያፈሩ ዛፎችም አይደሉም። እነርሱን የሚያበቅሉ፣ አብቅለውም ማሳደግ የሚችሉ ተቋማትን ይፈልጋሉ። እነዚህ ተቋማት ባልተገነቡበት፣ ተገንብተውም ባልዳበሩበት ሁኔታ የምንመኘውን ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሳይሆን የጠላነውንና የሸሸነውን ሥርዐት አልበኝነትና አፋኝነት አጭደን ምርቱን ማቀፋችን አይቀርም። እህሉን ስለፈለግነውና ስለዘራነው ብቻ አይበቅልም። መሬቱ እህሉን ለማብቀል የሚችል፣ ሰብሉም ተገቢው እንክብካቤ የሚደረግለት ከሆነ ብቻ ነው፣ ዛሬ ቡቃያ ሆኖ የሚያጓጓን የለውጥ ሰብል ነገ ሁላችንን ስንመኘው የኖርነውን የሥልጣኔና የብልጽግና ነዶ ሊያሳቅፈን የሚችለው።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተከለ ያለው አዲሱ የለውጥ እርምጃ አቅጣጫው በዚሁ የሚመራ ነው። ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሊሸከሙ፣ ሊያሳልጡ፣ ሊያሰፍኑና ሊያስከብሩ የሚችሉ ተቋማትን በመገንባት ላይ እንገኛለን። በተጓዳኝም ለተቋማቱ የሚመጥን አመለካከት ያላቸው ባለሞያዎችንና ቢሮክራቶችን መምረጥ፣ ማሠልጠንና መመደብ የሳንቲሙ ሌላኛው ገፅታ ነው። ውጤታማነትና ቅልጣፌን የሚያረጋግጥ ተደርጎ ሰሞኑን ያዋቀርነው አዲስ ካቢኔም ከዚሁ ዓላማና ግብ በመነጨ ነው። ምርጫ ቦርድ ነጻ፣ ተአማኒና ገለልተኛ እንዲሆን ለማድረግ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያ እየሠራን ነው። የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት በሠለጠነ መንገድ የዜጎችን መብትና ክብር ጠብቀው የሚፈለግባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ጠንካራ ሪፎርም በማካሄድ ላይ እንገኛለን። መከላከያችን በሁሉም መልኩ ኢትዮጵያን የሚወክልና የሚመስል፤ የዘመነና ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ሀገሪቱን ሊጠብቅ በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የበኩላችንን እየሰራን ነው። የፍትሕ ተቋማት ለዜጎች መብት መከበር የሚሠሩ፣ በገለልተኝነት፣ በሕግ-የበላይነትና በኅሊናቸው ልዕልና ብቻ እንዲዳኙ፣ በሕዝቡም ዘንድ የሚከበሩና የሚታፈሩ ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ የዚህ ዓመት አንዱና ዋናው ሥራችን ነው። በቅርቡም በፍትህ ዘርፉ ተከታታይ እርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል።

የትምህርት ሂደቱን የተሻለና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶለት በሚመለከታቸውም አካላት እንዲታይ ሠፊ የተግባር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን።
የትናንቱን ዝንፈት ከመጠገንና በጠንካራ መሰረት ላይ ከማነጽ ጎን ለጎን የዛሬው ግንባታ ከሥር ከሥሩ እንዲፋጠን፣ አሁን ላለው ትውልድ ሥራ መፍጠር፣ ኢኮኖሚው በሚገባ እንዲያንሠራራ ማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን መቋቋም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማብረድና እንዳይከሠቱ ማድረግ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ውጤታማ ማድረግ፣ ለነገ ፋታ የማይሰጡን ተግባራት ናቸው። ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ደግሞ ከፊታችን ተዘርግቷል።

የአገሬ ልጆች

በሶስት ግንባር ከከፈትነው ጦርነት ጋር የምናደርገው ትግል መደምደሚያው በድል እንደሚጠናቀቅ በፍጹም አልጠራጠርም።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጄኔራል ፓርክ፣ በጀርመን ሀገር በነርስነትና በመአድን ቁፋሮ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የዴያስፖራ ዜጎቻቸውን ደሞዝ በመያዣነት በመጠቀም ብድር መጠየቃቸው ይታወሳል። በሂደትም ተመፅዋች ሀገራቸውን ዛሬ ከእድገት ማማና ለጋሽ ሀገር ማድረግ ችለዋል።

የእኛ ትውልድ የምታኮራና አንጸባራቂ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ግዙፍ ኃላፊነት ከፊታችን ተዘርግቷል። ምናልባትም የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ ይሄንን ማድረግ ይቻለናል ወይ? የሚል ነው።

ያለጥርጥር አዎ! ይቻለናል! ነው መልሱ።

ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር፣ ባለ ክቡር ታሪክ፣ የጠቢባንና የሊቃውንት መፍለቂያ ምድርን፣ የማይበገርና የማይናወጥ ሕዝብ ይዞ መሸነፍ የማይታሰብ ነው። ከተባበርንና አንድ ከሆንን፤ በትንንሾቹ ጉዳዮች ላይ የተጣዱ ትኩረቶቻችንን ወደታላላቆቹ ቁምነገሮች መልሰን ትልቁ ሥዕል ላይ ካተኮርን፣ ዛሬን ለነገ ስንል ችለን፤ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት ከቆረጥን፤ ጉልበታችንን በማይረቡ ነገሮች ላይ ካላፈሰስን፣ ምንጮቹን ጅረቶች፣ ጅረቶቹን ወንዞች፣ ወንዞችንም ባሕሮች ለማድረግ ቆፍጠን ብለን ከሠራን ድላችን ሩቅ አይሆንም፣ ይቻላል። የድል ነጋሪትም ይጎሠማል።

የተከበራችሁ የሀገሬ አምባሳደሮች

እኔ ዛሬ እዚህ የቆምኩት እናንተ በአውሮፓ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንድሆናችሁ ከልቤ ስለማምን እና ከኮሪያውያን ስለተማርኩም ጭምር ነው። የሀገራችሁ ነገር ስለሚያሳስባችሁ ቀን በሥራ ብትደክሙም ሌሊቱን በሀሳብ ተጉዛችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትብሰለሰሉና ላይ ታች ስትሉ እንደምታድሩ በሚገባ አውቃለሁ። እዚህ ማስናችሁ ከምታገኙትን፣ ሀገር ቤት ያለው ዘመዳችሁ እኩል ተካፋይና የወዛችሁ ተጠቃሚ መሆኑም ድንቅ ነው። ለራሳችሁ በኪራይ ቤት እየኖራችሁ የወላጆቻችሁን ቤት ትሠራላችሁ። እናንተ ለመማር ያላችሁን ዕድል አሳልፋችሁ ቀን ከሌት እየለፋችሁ ታናናሾቻችሁን ታስተምራላችሁ። ይህንን ሁሉ የምታደርጉት በእርግጥ ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው። ስለዚህም አምባሳደሮች ብላችሁ አይበዛባችሁም።

ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓ ጋር ያላቸው ትውውቅ ከ 500 ዓመታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በዚህ ዕድሜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በተደራጀና በአሰራር በተደገፈ መልኩም ባይሆን ለሀገራቸው የሚሆን ብዙ ነገር እየቀሰሙ በነጠላና በቡድን በመሆን ወደሃገራቸው ተመልሰዋል። እናንተም እንደነርሱ ለሀገራችሁ የሚበጀውን ሥራ ሁሉ ለመስራት መትጋት ይኖርባችኋል። ዕውቀትን አሻግሩ። ለሀገራችሁ የገቢ ምንጭ ፍጠሩ። አዳዲስ አሠራሮችን አምጡ፤ እንዲሆን የምትመኙትን በጥልቅ መረዳት ጨብጣችሁ ወደሃገራችሁ ኑና ተግባራዊ አድርጉት። ከማንም አትጠብቁ። ኢትዮጵያ የእናንተ ናት። ማንም ቢሆን የእናትና የአባቱን ቤት በማገዝ እንጂ በማማረር ለውጦ አያውቅም። ኢትዮጵያም ይሄንኑ ትፈልጋለች። ማን ለማን ቅሬታ ያቀርባል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ማንን ያማርራል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ለማን ሥራውን ይተወዋል? ሁላችንም እኛው ነን። አንድ ቤተሰቦች ነን።

አምባሳደሮቼ ሆይ!

አሁን በአውሮፓ ቅዝቃዜው እየጀመረ ነው። ከክፍለ ዘመናት በፊት በድፍን አውሮፓ በቅዝቃዜው ጦስ ብዙ ሕዝብ ያልቅ ነበር። የሕልውና ጉዳይ ነውና በችግሩ ከመረታት ይልቅ፣ ችግሩ ወደ ብልሃት መራቸው። የበረዶውን ወቅት በማሞቂያና በበረዶ መጥረጊያ የሚያልፉበትን ብልሃት ቀየሱ። የሀሩሩንም ግለት ለማብረድ የአየር ማቀዝቀዢያን ፈለሰፉ። በችግር መቆዘምና ማማረር ሳይሆን ችግርን እንደ ዕድገት መሰላልና ድልድይ በማየት ጉዞን በፍጥነት ወደ ላይና ወደ ፊት ማድረጉ ይበጃል። ስለዚህ፣አንድ ሆነን ዛሬ እንነሣ! የምንተኛበት ሳይሆን የምንነቃበት… የምንከፋፈልበት ሳይሆን ያለንንና የሆነውን ሁሉ በአንድነት አጣምረን የምንነሳበት ጊዜ ነው። ትናንት ከኛ ውጭ ነው። ቆርጠን ከተነሳንና ከተጠቀምንበት ያለንም ያለነውም ዛሬ ላይ ነው። የማግለል ሳይሆን የማቀፍ፣ የመንቀፍ ሳይሆን የማበረታታት፣ ሁሉን ለኔ የሚል ሳይሆን የመተሳሰብ ባህል ከፈጠርን ደግሞ ገና ያልተነካው ነገም አንጡራ ሀብትና ወርቃማ ዕድል ሆኖ ከፊታችን ይጠብቀናል። ዛሬ ላይ በርትተን በመሥራት የነገን የሰለጠነ ማህበረሰብና የበለጸገች ውብ ኢትዮጵያን አብረን እንገንባ።
ከዐሥር ዓመት በኋላ ችግሮቿን ሁሉ ትዝታ ያደረገች፣ የማትፈርስ፣ የማትቀለበስና ወደ ኋላ የማትመለስ… ለሁላችንም የምትበቃ፣ ለሌሎች የምትተርፍ፣ የአፍሪካ ኩራት፣ የዓለም ፈርጥ የሆነች ኢትዮጵያን አያለሁ።
ተስፋ አደርጋለሁ።

በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች ሀገርና ቀያቸውን ጥለው በየሰዉ ሀገር የተበተኑ ህዝቦቿ በሀገራቸው በፈቀዱበት ቦታና መንገድ በፍቅርና በመልካም ጉርብትና በሀገራቸው ዘና ብለው የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ተስፋ አደርጋለሁ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች አውሮፓ መጥተው ለማግኘት ለሚያልሙት ያልርተረጋገጠ ቀቢጸ ተስፋ የሰሀራን በርሃ አቋርጠው፣ የሜዲትራኒያንን ባህር ከፍለው የሚነጉዱበት ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል። ፍሰቱ ወደ አውሮፓ መሆኑ ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ይቀለበሳል። ልጆቻችን ወደ አውሮፓ ለጉብኝት እንጂ ለስደት የሚመጡበት ጊዜ ያበቃል። 

ተስፋ አድርጋለሁ።

ዛሬ በመረጥነው በጎ ጎዳናና በፈጸምነው ሰናይ ምግባር ልጆቻችንም በክብር ስማችንን እንደሚያነሡ አምናለሁ።

ተስፋ አደርጋለሁ።

ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በእግራችን እየተራመድን የዛሬዋን ቀን በደስታ አስታውሰን እንኳንም ለዚህች ታላቅ ሀገር ደከምን ብለን ደስ የሚለን ቀን ይመጣል።

ተስፋ አደርጋለሁ።

ሁላችንም ወደ ልቡናችን ተመልሰን፣ የትናንቱን በዕርቅና በይቅርታ ዘግተን፣ የነገውን በተስፋና በፍቅር ሰንቀን፣ የምንኮራባትን ልዩ ሀገር እንገነባለን።

ተስፋ አደርጋለሁ። አምናለሁም።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
አመሠግናለሁ
ኢሽ ዳንከ ኢኔን!

Tallest building in Addis adds two more stories

በኢትዮጵያ ረጅሙ ህንፃ የ2 ወለል ከፍታ ጭማሪ አደረገ
************************************************* 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋና መስሪያ ቤትነት በአዲስ አበባ እያስገነባው የሚገኘውን ህንፃ ከ46 ወለል ወደ 48 ወለል ከፍ አደረገ፡፡

ባንኩ የዋና መስሪያ ቤቱ ግንባታ የወለል ከፍታ እንዲጨምር ያደረገው ቀድሞ በነበረው ባለ 46 የወለል ከፍታ ድዛይን ላይ ማሻሻያ በማድረግ ነው፡፡

እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ህንፃው ከ200 ሜትር በላይ በሚሆነው ርዝመቱ ከምስራቅ አፍሪካ የሚወዳደረው የለም ተብሏል፡፡

ህንፃውን ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ እንደሚፈጅም ነው ከባንኩ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

በቻይና የመንግስት ግንባታ ኮርፖሬሽን (CSCEC) በ150 ሺህ ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው ይኸው የምስራቅ አፍሪካ ረጅሙ ህንፃ በተጨማሪም 2 ባለ 5 ወለል የስብሰባ ማእከልና አጠቃላይ አገልግሎት ህንፃዎችን ያካተተ ዘመናዊ ህንፃ ነው፡፡

በዚሁ የህንፃ ግንባታ ከወለል በታች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የምድር ውስጥ ወለሎችንም ያቀፈ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ማእከል በሆነው የብሄራዊ ቲያትር አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ህንፃው፤ በአራቱም ማዕዘናት ከተማዋን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

የህንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ በቱሪስት ከሚጎበኙ ቦታዎች አንደኛው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የህንፃው የመጨረሻው የወለል ክፍልም ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፎቶግራፎቹ በመገንባት ላይ ከሚገኘው ህንፃ አናት ላይ የሚታየውን የአዲስ አበባ ከተማ ገፅታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በናትናኤል ፀጋዬ

Visa on arrival to All African in Addis Ababs

ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካ ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ መስጠት ጀምራለች
*************************

ኢትዮጵያ ከጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ህዝቦች በቦሌ አለም ዓቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ  ሂሩት ዘመነ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም የአገልግሎቱን መጀመር በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለህብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች እንዲሁም ለህብረቱ ኮሚሽንና የተ.መ.ድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮችና ባልደረቦች ገለፃ አድርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ በህብረቱ 2063 አጀንዳ የበለጠ ትኩረት የተሰጠው የበለጸገች፣ የተዋሃደችና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን የመፍጠር የቆየ ራዕይ እውን እንዲሆን እየሰራች መሆኑን ገልጸው  በኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አመራር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የራዕዩ አንድ ዋና አካል የሆነውን ነፃ አህጉራዊ የሰዎች ዝውውር እውን የማድረግ እንዲሁም አዕምሮዎችን ለገንቢ ሃሳብና ገበያዎችን ለጋራ ንግድ ክፍት የማድረግ ቁልፍ የህብረቱ ግቦችን ለማሳካት አገልግሎቱ እንዲጀመር መደረጉን አስረድተዋል።

አገራችን ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የአፍሪካ አገራትን መቀላቀሏ የህብረቱን የነፃ ንግድ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ፍሰትና ትስስሮችን የሚያሰፋና የአህጉራዊ ውህደት አጀንዳውን ተፈፃሚነት የሚያፋጥን እንደሚሆንም ገልጸዋል። አህጉራዊ የአየር ትራንስፖርትና የመሰረተ ልማት ትስስሮች እንዲፋጠኑ እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱና ሴቶች የአገር ፕሬዝዳንትነት፣ የካቢኔ ሹምነት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ከፍተኛ ሃላፊነቶችን በስፋት እንዲይዙ ማድረጋቸውም የህብረቱ ቁልፍ አጀንዳዎች የሆኑትን አህጉራዊ የወጣትና ጾታዊ ተሳትፎ የማሳደግ አጀንዳዎች ከማሳካት አንጻር በሞዴልነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ አገራችን አገልግሎቱን መጀመሯ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናነቷን እንደሚያሳድገው ገልጸው፣ ሌሎች የህብረቱ አባል አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ የአፍሪካ ኩራት እንደመሆኑ ከህብረቱ አባል አገራት ቁጥር በላይ 59 የአፍሪካ መዳረሻዎች ያሉት መሆኑን ጠቁመው የተጀመረው የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን በ59ኙም የአየር መንገዱ የአፍሪካ መዳረሻዎች በሚገኙ ጽ/ቤቶቹ ከተጓዦች የቪዛ ማመልከቻና ክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማስጨረስ አገራዊና አህጉራዊ ግዴታውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ በበኩሉ ለአገልግሎቱ መሳለጥ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። በተጨማሪም አፍሪካውያንን ጨምሮ ለተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግልጋሎቶችም ሆነ ሌሎች ቋሚ ስራዎች፣ ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና ወዘተ ለሚመጡ የሌላ አገር ዜጎች ከ5-10 አመታት የሚያገለግል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

የህብረቱ አባል አገራት ተወካዮች በበኩላቸው አገራችን የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑንና ቀሪ አባል አገራትም ተመሳሳይ መንገድ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

አገራችን ከመላው አለም ወደ አገራችን ለቱሪዝም መምጣት ለሚፈልጉ ሁሉ በኢንተርኔት ማመልከቻ አቅርበው ሲፈቀድላቸው ተገቢውን ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ሲፈጽሙ የመዳረሻ ቪዛ የሚያገኙበትን አሰራር መጀመሯ የሚታወስ ነው።

ምንጭ:-  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Thursday, November 1, 2018

Ethiopia swears in first female Supreme Court chief

(CNN) - Human rights lawyer Meaza Ashenafi was sworn in Thursday as the head of Ethiopia's Supreme Court by the country's parliament in a wave of appointments for women in top government positions.

Prime Minister Abiy Ahmed nominated Meaza, the country's chief of staff announced. The Ethiopian leader has pushed for more female representation in his Cabinet.

Tuesday, October 30, 2018

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ ሩሲያ መብረር ይጀምራል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ ሩሲያ መብረር ይጀምራል
*****************************************************
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ ሩሲያ ርዕሰ ከተማ ሞስኮ የቀጥታ በረራ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በቆዳ ስፋቷ የአለም ግዙፍ ሀገር ወደ ሆነችው ሩሲያ የሚጀመረው የበረራ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የቀጥታ በረራ አገልግሎትም እጅግ ዘመናዊ በሆነው 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በሳምንት ለሶስት ቀናት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡ 

ከነገ ጀምሮ የሚጀመረው በረራም በአፍሪካ ሀገራትና በሩሲያ መካከል ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እንዲቀላጠፍ ብሎም እንዲጎለብት ያግዛል ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡

በዚህም ረገድ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሁም የሩሲያ ቱሪስቶች አፍሪካ ሀገራትን እንዲጎበኙ ምቹ እድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ116 አለም አቀፍ መዳረሻዎች አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድንገት በጀርመን በርሊን አደባባይ


ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበርሊን ከታደሙበት ስብሰባ አፍታ ወስደው በበርሊን ከተማ ብራንደርን ቡርግ አደባባይ የተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸውን በድንገት አግኝተዋቸዋል፡፡

የጀርመን ድምፅ  ራዲዮ ዶች ቬሌ  እንደዘገበው  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገት ከጠባቂዎቻቸው እና ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ወደ አደባባይ ብቅ ሲሉ የተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን በጩኸት ድጋፋቸውን ገልፀውላቸዋል።
ቅጽበቱን በፎቶ እነሆ፡፡

በምዕራብ ወለጋና በቄለም ወለጋ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት እጃቸውን መሰብሰብ አለባቸው:- አቶ ለማ መገርሳ

በምዕራብ ወለጋና በቄለም ወለጋ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት እጃቸውን መሰብሰብ አለባቸው:- አቶ ለማ መገርሳ
********************************

በምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች በኦነግ ስም ታጥቆ የሚንቀሳቀስና ህዝቡን ለችግር እየዳረገ ያለው አካል እጁን መሰብሰብ አለበት ብለዋል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፡፡

ፕሬዝዳንቱ መንግስት ይህንን ድርጊት በትዕግስት ሲከታተል መቆየቱን  ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ የህዝቡ ደህንነት እንዲጠበቅና ሕግ እንዲከበር እንሰራለን ብለዋል፡፡

ህዝቡም ሆነ የአገር ሽማግሌዎች በዚህ ድርጊት  የተሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀዋል አቶ ለማ መገርሳ፡፡

ምንጭ: OBN

Monday, October 29, 2018

ፈረንሳይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች

ፈረንሳይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች
*************************************************************************************
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ በፓሪስ መክረዋል፡፡

ሀገራቱ የቆየ ወደጅነታቸውን በማጠናከር ለተሻለ ለውጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ሰላምና ደህንነት፣ንግድና ኢንቨስትመንት ፣ ትምህርትና ባህል ደግሞ በጋራ ለመስራት ከተስማሙባቸው ዘርፎች ይጠቀሳሉ᎓፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሁለትዮሽ ውይይታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ  እንዳስታወቁት የሀገራቱን ትብብር የበለጠ ለማሳለጥ ይሰራል፡፡

ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃ ያላትን አቅም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ እንድታውለው የቀረበላትን ጥሪ እንደተቀበለች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፀዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የመጣውን ሰላም በማስቀጠል በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ሰላም እንዲጠናከር ለማድረግ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱንም አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ሀገራቸው ዠግጁ እንደሆነች ገልፀዋል፡፡

በቴሌኮም በትራንስፖርት በመሰረተልማት ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት  እንዳላትም እንዲሁ፡፡

ከቀጠናው ሰላም ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እያደረጉ ያሉትን ተግባር እንደግፋለን እናደንቃለንም፤በተለይ በሳቸው ተነሳሽነት በኢትዮጵያና በኤርትራ የተፈጠረውን ሰላም በተመለከተ ልዩ አክብሮት አለን ፤ቀሪው የሰላም ሂደት የተሳካ እንዲሆንም ድጋፍ እናደርጋለን ፤ከኤርትራ ከጅቡቲም ሆነ ከሌሎች የቀጠናው ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ እየፈጠረች ያለቸውን የሰላምና የትብብር መንፈስ እንደፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን እንደ አውሮፓ ህብረት የምንደግፈው ነው ብለዋል ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፡፡

ከሁለት ወራት በኋላም የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከር ወደ ኢትዮጵያ እነደሚመጡም ተነግረዋል፡፡
በብሩክ ያሬድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፈረንሳይ ፓሪስ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፈረንሳይ ፓሪስ ገቡ
************************
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለስራ ጉብኝት ፈረንሳይ ፓሪስ ገብተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ቆይታቸው ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዶ/ር ዐቢይ ከፈረንሳይ ጉብኝት በኋላ ወደ ጀርመን ያቀናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሪፖርተራችን ብሩክ ያሬድ ከፓሪስ ዘግቧል፡፡

ፎቶ:- አቶ ፍጹም አረጋ፣ ብሩክ ያሬድ

ኮ/ል ጎሹ ወልዴ አዲስ አበባ ገቡ

ኮ/ል ጎሹ ወልዴ አዲስ አበባ ገቡ
**********************************
በደርግ ዘመነ መንግስት የአገራችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የትምርት ሚኒስትር የነበሩት ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ዛሬ አዲሰ አበባ የገቡ ሲሆን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነና እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳ/ጀነራል አቶ ነብያት ጌታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርግውላቸዋል።

የቀድሞው ሚኒስትር በቦሌ ዓለምአቀፍ አየር መንገድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የደርግን አገዛዝ በመቃወም ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁና ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉ ጀምሮ ላለፉት 32 አመታት የአገራቸውን መሬት ሲረግጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልጸው አመጣጣቸው የአገራችንን አጠቃላይ የለውጥ ሂደት ለማየት፣ ለረጅም ጊዜ የናፈቋቸውን ዘመድ ወዳጆች ለማግኘትና የተጀመረውን የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር ሂደት በሚችሉት መጠን ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ምንም አይነት ፖለቲካዊ ውድድር የማድረግም ሆነ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት የለኝም ያሉት ኮ/ል ጎሹ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተጀመረው የሰላም፣ የእርቅና የመደመር እንቅሴቃሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በመሆኑ እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊደግፈው እንደሚገባ በማመን መምጣታቸውን ጠቁመው ለዚህም ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወጣቱ የሰላምን አስፈላጊነት በሚገባ ተገንዝቦ ለግጭት ከሚዳርጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርበው ማንኛውንም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መፍትሄ ማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለዚህም ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራትና ለሰላማዊ ሂደቱ መጎልበት የተቻላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃል ገብተዋል።

ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Sunday, October 28, 2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመጀመርያ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በፈረንሳይ ለመጀመር ነገ ወደ ፓሪስ ያቀናሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመጀመርያ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በፈረንሳይ ለመጀመር ነገ ወደ ፓሪስ ያቀናሉ።
*******************************************************************ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ቆይታቸው ከፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይመክራሉ።

የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ እንዲሁም በፈረንሳይ ያለውን ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ክህሎት የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለመታደግ መዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ይወያያሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፈረንሳይ ያቀኑት ኢማኑኤል ማክሮን ከወራት በፊት ያቀረቡላቸውን ግብዣ ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ከፓሪስ ቆይታ በኋለ ወደ ጀርመን በርሊን በማቅናት  የቡድን 20 አባል ሀገራት በሚያዘጋጁትና በአፍሪካ ጉዳይ ላይ በሚመክረው ኮምፓክት አፍሪካ ጉበኤ ላይ ይሳተፋሉ።

በጀርመን አነሳሽነት የተቋቋመው ይህ የአፍሪካ የልማት ድጋፍ መርሐግብር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ ሀገራትን ማዕከል ያደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በጀርመን ቆይታቸው ከመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት የልማት ትብብር የበለጠ ለማጠናካር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይወየያሉ።

ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ከ2018 እስከ 2020 የሚቆይ የ213 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ትብብር በቅርቡ መፈራረሟ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፍራንክ ፈርት በማምራትም አንድ ሆነን አንነሳ ነገን እንገባ በሚል መርህ በተዘጋጀው የኢትዮጵያውያን መድረክ ላይም ይገኛሉ።

በዚህ መድረክ ከ20ሺ በላይ ከመላው አውሮፓ የተውጣጡ ኢትየጵያውያን ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ይወያያሉ በሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማት ላይ በሚሳተፉበት መንገድ ላይም ይመክራሉ  ።

በብሩክ ያሬድ

Thursday, October 18, 2018

Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed has said that some of the soldiers who entered the grounds of his office last week had wanted to kill him.

Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed has said that some of the soldiers who entered the grounds of his office last week had wanted to kill him.

At the time, he defused the situation by ordering them to do press-ups and joining in.

Mr Abiy and the soldiers were seen laughing but he told parliament that "inside I was very unhappy".